በኢራቅ በመኪና ላይ በተጠመደ የቦምብ ፍንዳታ በትንሹ 20 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 12፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሰሜን ኢራቅ ቱዝ ኩርማቱ ከተማ በመኪና ላይ በተጠመደ የአጥፍቶ ጠፊዎች የቦምብ ጥቃት በትንሹ የ20 ሰዎች ህይወት ማለፉን የህክምና መረጃዎች ገልፀዋል።

ዓረቦች፣ ኩርዶች እና ቱርኮች ተቀላቅለው ከሚኖሩባት ኪርኩክ ከተማ በስተደቡብ በሚገኘው በአንድ የገበያ ቦታ አቅራቢያ ዛሬ በደረሰው የቦምብ ፍንዳታ፥ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውም ተነግሯል።

የኢራቅ ጦር በኩርድ የፔሽሜርጋ ተዋጊዎች ላይ ጥቃት በመክፈት በነዳጅ ሀብታም የሆነችውን የኪርኩክ ግዛት መቆጣጠሩ ይታወሳል።

ቱዝ ኩርማቱ ከተማ የኩርድ ህዝብ ከኢራቅ ለመነጠል ያደረገውን ህዝበ ውሳኔ ተከትሎ የተቀሰቀሰውን ብጥብጥ ለማርገብ የኢራቅ መንግስት የጦር ኃይሉን ካሰማራባቸው በርካታ ከተሞች አንዷ ነች።

ዛሬ ለደረሰው ጥቃት ሃላፊነት የወሰደ አካል እስካሁን አልታወቀም።

ምንጭ፦ አልጀዚራ