ሮበርት ሙጋቤ ስልጣናቸውን በራሳቸው ፈቃድ ለቀቁ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 12፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የዚምባብዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ስልጣናቸውን በራሳቸው ፈቃድ መልቀቃቸውን የሀገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ጃኮብ ሙዴንዳ ተናግረዋል።

ሙጋቤ በፃፉት መልዕክት ውሳኔያቸው በፈቃደኝነታቸው እና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር ያደረጉት መሆኑን ገልፀዋል።

አስገራሚው የሙጋቤ ውሳኔ ክስ ተመስርቶባቸው ከስልጣናቸው እንዲነሱ የነበረውን ሂደት እንዲቋረጥ አድርጓል።

የሙጋቤን በፈቃደኝነት ከስልጣን መልቀቅ ተከትሎ ዚምባብዌያውያን በመንገዶች ላይ ወጥተው ደስታቸውን እየገለፁ ነው።

የሀገሪቱ የፓርላማ አባላት ፕሬዚዳንቱን ለመክሰስ ስብሰባ በጀመሩበት ወቅት ሙጋቤ በራሳቸው ፈቃድ ከስልጣናቸው መልቀቃቸው ይፋ ሲደረግ አባላቱ በደስታ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሲጮሁ ተሰምተዋል።

የሙጋቤን በፈቃደኝነት ከስልጣን መልቀቅ ተከትሎ ዚምባብዌያውያን በመንገዶች ላይ ወጥተው ደስታቸውን እየገለፁ ነው።

ሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ አሁን ላይ 93ኛ ዓመት እድሜያቸው ላይ ሲሆኑ፥ ዚምባብዌን ከፈረንጆቹ 1980 ጀምሮ ላለፉት 37 ዓመታት መርተዋታል።

ከተወሰኑ ቀናት በፊት የሀገሪቱ ጦር ስልጣን መቆጣጠሩን ቢገልፅም፣ በርካታ ዚምባብዌያውያን አደባባይ ወጥተው አዛውንቱ መሪ ስልጣናቸውን እንዲለቁ ቢጠይቁም ሙጋቤ ግን ስልጣኔን አልለቅም ማለታቸው ይታወሳል።

የፕሬዚዳንትነት ስልጣኑን ማን እንደሚረከብ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ሆኖም በሀገሪቱ ህገ መንግስት መሰረት የውቅቱ ምክትል ፕሬዚዳንት በፕሬዚዳንትነት መተካት አለባቸው ይላል።

 

 

ምንጭ፦ቢቢሲ