ናይጀሪያ ቦኮሃራምን የማጥፋት ዘመቻን የሚመሩትን የጦር ጀኔራል ከሀላፊነት አነሳች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የናይጀሪያ ቦኮሃራምን የማጥፋት ዘመቻን የሚመሩትን የጦር ጀኔራል አታሂሩ ኢብራሂምን ከሃላፊነታቸው አነሳች።

የሀገሪቱ ጦር ጀኔራሉን ያሰናበታቸው፥ የቦኮሃራም ፅንፈኛ ሃይሎች ባለፈው ወር በሰሜናዊ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል 50 ሰዎችን የገደለበትን ጨምሮ በርካታ ጥቃቶችን ማድረሱን ተከትሎ ነው።

ሆኖም ለሜጀር ጀኔራል አታሂሩ ከስልጣን መነሳት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ይፋዊ መግለጫ አልተሰጠም።

የናይጀሪያ ጠቅላይ ጦር ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ቱኩር ቡራታይ የቦኮሃራም መሪ አቡበከር ሼካው መገደሉን ወይም በህይወት መኖሩን በ40 ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቁ፥ ባለፈው ሃምሌ ለሜጀር ጀኔራል አታሂሩ ትዕዛዝ ሰጥተዋቸው ነበር።

ቦኮሃራም ከፈረንጆቹ 2009 ጀምሮ በሰሜናዊ ምስራቅ ናይጀሪያ ጥቃት ከጀመረ ወዲህ በትንሹ 20 ሺህ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፥ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ በሽብር ቡድኑ ታግተዋል።

የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙሃመዱ ቡሃሪ በፈረንጆቹ 2015 ወደ ስልጣን ሲመጡ፥ የሽብር ቡድኑን እንደሚያስወግዱት ቃል ገብተው ነበር።

ወደ ስልጣን ከመጡ ከሰባት ወራት በኋላ የናይጀሪያ ጦር በርካታ ይዞታዎችን ከቦኮሃራም ነፃ ማውጣቱን ተከትሎ የሽብር ቡድኑ ተሸንፏል ብለው መግለፃቸው ይታወቃል።

የሆነው ሆኖ ቦኮሃራም በተንሳራፋበት የሰሜናዊ መስራቅ ናይጀሪያ አካባቢ ዛሬም ድረስ የቦምብ እና የተኩስ ጥቃቶችን እያደረሰ ነው።

ሜጀር ጀኔራል አታሂሩ ኢብራሂም የፀረ ቦኮሃራም የማጥቃት ዘመቻን እንዲመሩ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ግንቦት ወር ላይ ነበር የተሾሙት።

አሁን ላይ ከሃላፊነታቸው የተነሱ ሲሆን በምትካቸውም የናይጄሪያ ልዩ ወታደራዊና እና ፖሊስ ሃይሉን የሚመሩት ጀኔራል ኒኮላስ ሮጀርስ ፀረ ቦኮሃራም ዘመቻን እንዲመሩ ተሹመዋል።

 

 

 

 

ምንጭ፦ቢቢሲ