አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ኤምባሲዎቿን ደህንነት ለማስጠበቅ የባህር ሃይሏን ላከች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ መሆኗን እውቅና መስጠታቸውን ተከትሎ አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ኤምባሲዎቿን ደህንነት ለማስጠበቅ የባህር ሃይል መርከቧን ወደ አከባቢው ላከች።

የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኮሎኔል ማይክ አንድሬውስ የሀገሪቱ ወታደራዊ ኃይል በተጠንቀቅ ላይ ነው ብለዋል።

ትራምፕ በቴል አቪቭ የሚገኘውን የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ እየሩሳሌም እንደሚዛወር ማሳወቃቸውን ተከትሎ ግጭት የሚከሰት ከሆነ ምላሽ ለመስጠት በንቃት ክትትል እንደሚያደርግ ነው የጠቆሙት።

ስለሚወሰዱ የደህንነት እርምጃዎች በዝርዝር ያልተናገሩት ቃል አቀባዩ፥ የመከላከያ ሚኒስቴር በመላው ዓለም በሚገኙ አሜሪካ የኤምባሲ ሰራተኞች እና የሀገሪቱ ጥቅሞች ላይ ስጋት እንዳይኖር እየሰራ መሆኑን አንሰተዋል።

የአሜሪካ ባለስልጣናት የባህር ሃይል የፀረ ሽብር ቡድን በመካከለኛው መስራቅ በሚገኙ የሀገሪቱ ኤምባሲዎች ለመላክ መታቀዱን በቅርቡ መግለፃቸው ይታወቃል።

የበርካታ ሀገራት መሪዎች ትራምፕ ትናንት እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ናት የሚል እውቅና መስጠታቸውን ኮንነዋል።

በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል የሚደረገው የሰላም ድርድር ላይ እንቅፋት የሚፈጥር ውሳኔም ነው ያሉት።

የፕሬዚዳንቱ እርምጃ በመካከለኛው ምስራቅ ግጭት እንዲቀሰቀስ ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋትም ፈጥሯል።

ምንጭ፦www.middleeastmonitor.com