ፍርድ ቤቱ በእነ አቶ በቀለ ገርባ የክስ መዝገብ የሚገኙ ተከሳሾች የተለያዩ ምስክሮች ይቅረቡልን በማለት ባቀረቡት ጥያቄ ላይ ትዕዛዝ ሰጠ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የወንጀል ችሎት በእነ አቶ በቀለ ገርባ የክስ መዝገብ የሚገኙ ተከሳሾች የጠቅላይ ሚኒስትሩን የፓርላማ መግለጫና የፌደራል መከላከያ ምስክሮች ይቅረቡልን በማለት ባቀረቡት ጥያቄ ላይ ትዕዛዝ ሰጠ።

አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ አራት ተከሳሾች የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በፓርላማ የሰጡት መግለጫ ከኦሮሚያ ቴሌቪዥንና ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እንዲቀርብላቸውና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች የመከላከያ ምስክሮች ፍርድ ቤት ይቅረቡልን በማለት ጥያቄ አቅርበው ነበር።

ፍርድ ቤቱም የተከሳሾች ጥያቄ ላይ በዛሬው እለት ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን፥ በተከሳሾች የተጠየቀውን ማስረጃ ማቅረቡ አግባብ አይደለም ብሏል።

ከዚህ ባለፈም የመከላከያ ምስክሮችን በፖሊስ እንዲቀርቡ ማዘዙ ተገቢ አይደለም ሲልም ብይን ሰጥቷል።

የፍርድ ቤቱን ብይን ተከትሎም ተከሳሾች ተቃውሞ በማሰማት ችሎቱን አውከዋል።

ፍርድ ቤቱ የተሰጠውን ብይን የተቃወሙት ተከሳሾች፥ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጭ ያሉ የመከላከያ ምስክሮች ለመመስከር ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ሳለ የፍርድ ቤቱ ብይን አግባብ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም በቀጣይ ፍርድ ቤቱ የሚሰጠውን ቀጠሮ አንሰማም በማለትም ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ይሁንና ፍርድ ቤቱ አቃቢ ህግና የተከሳሽ ጠበቆችን በማስቀረብ ፍርድ ለመስጠት ለጥር 10 ቀን 2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ተከሳሾች ላይም ችሎት በማወክና ዳኛ በመሳደብ እያንዳንዳቸው ላይ የ6 ወር የእስራት ቅጣት አስተላልፏል።

 

በታሪክ አዱኛ