የቅማንት ህዝብ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጉዳይን የመጨረሻ እልባት የሚሰጥ ውይይት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 3 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የቅማንት ህዝብ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጉዳይን የመጨረሻ እልባት የሚሰጥ ውይይት በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው።

ውይይቱ ላይ የቅማንት ህዝብ የራስ አስተዳደር ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ያለመ ነው ተብሏል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የቅማንት ህዝብ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄን ለመፍታት መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ የቅማንት ህዝብ የራስ አስተዳደርን ለማቋቋም ያላስቻሉ ልዩነቶችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

አሁን ላይ የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ለጉዳዩ የመጨረሻ እልባት ለመስጠት እየሰራ ነው ብለዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ብናልፍ አንዷለም በበኩላቸው፥ ጉዳዩን መፍትሄ ለመስጠት ህዝባዊ ውይይት በማካሄድ መንግስት ከተቋቋመው ጥምር ኮሚቴ ጋር ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በህዝበ ውሳኔ መግባባት ከተደረሰበት በኋላ ተፈጻሚ ያልሆነው የቅማንት ህዝብ የማንነትና የራስ አስተዳደር አለመተግበር ስጋቶች ፈጥሮ መቆየቱንም አቶ ብናልፍ አንስተዋል።

በዚህ ሳቢያ የህዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን የማስከበር ጥያቄ እንዳይመለስ፣ አካባቢው ላይ ስጋት መደቀኑንና ህዝቡ ወደ ልማት እንዳይገባ ማድረጉን ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻርም የራስ አስተዳደሩን በፍጥነት ተግባራዊ በማድረግ የህዝቡን ጥያቄ መመለስ እንደሚገባ በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።

 

በምናለ አየናቸው