የጀርመን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምር መንግስት ለመመስረት ተስማሙ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 4 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የጀርመን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምር መንግስት ለመመስረት መስማማታቸውን አስታወቁ።

የመራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ፓርቲ ክርስቲያን ዴሞክራትስና የእርሳቸው ተቀናቃኝ ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ጥምር መንግስቱን ለመመስረት ተስማምተዋል።

ሁለቱ ፓርቲዎች ለረጅም ጊዜ ሲያደርጉት ከነበረው ድርድር በኋላ ጥምር መንግስቱን መመስረት በሚያስችላቸው ነጥቦች ላይ መስማማታቸውን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በቀጣዮቹ ሳምንታትም ስለ ጥምር መንግስቱ አጠቃላይ ምስረታ ይወያያሉ ተብሏል።

ባለፈው መስከረም ወር በተካሄደ የሃገሪቱ ጠቅላላ ምርጫ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል።

ይሁን እንጅ ወግ አጥባቂ ፓርቲያቸው ራሱን ችሎ መንግስት መመስረት የሚያስችለውን ድምጽ አላገኘም ነበር።

ይህን ተከትሎም ሜርክል ከተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጋር ጥምር መንግስት ለመመስረት ረጅም ድርድር ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

ድርድሩ ባለፈው ህዳር ወር ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፥ እርሳቸውም ከጥምር መንግስት ይልቅ በድጋሚ ምርጫ ቢካሄድ እንደሚመርጡ ተናግረው ነበር።

ሜርክል በወቅቱ ሃገራቸው ለምታሳልፈው እያንዳንዱ ውሳኔ አብላጫ ድምፅን ከመጠቀም ይልቅ፥ ጠንካራና የተረጋጋ መንግስት ያስፈልጋታል በማለት ነበር የድጋሚ ምርጫውን ከጥምር መንግስት ምስረታው ይሻላል ያሉት።

ሁለቱ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ባደረጓቸው ድርድሮች፥ ግብር፣ የስደተኞች ጉዳይ እና የአየር ንብረት ፖሊሲዎች የልዩነቶቻቸው መንስኤዎች ነበሩ።

በሃገሪቱ የሚገኙ የሶሪያ ስደተኞች ቤተሰቦቻቸውን ወደ ጀርመን እንዲያመጡ ይፈቀድ አይፈቀድ የሚለው ነጥብም ዋናው የልዩነት መነሻ እንደነበር አይዘነጋም።

ሶሻል ዴሞክራት (ኤፍ ዲ ፒ) የሶሪያ ስደተኞች ቤተሰቦቻቸውን እንዳያመጡ የሚከለክለውን ህግ ሲቃወም፥ ሜርክል ደግሞ እንዲራዘም እንደሚፈልጉ ሲገልጹ ነበር።

አሁን ላይ ግን በእነዚህ ልዩነቶቻቸው ላይ ስለመስማማታቸው እየተነገረ ነው።

አጠቃላይ የጥምር መንግስት ምስረታው ሂደትና ቀጣይ ውይይቶችም በቀጣዮቹ ሳምንታት ይካሄዳሉ።

 

ምንጭ፦ ሬውተርስና ቢቢሲ