የደቡብ ክልል ምክር ቤት የሀዋሳ ከተማን የክፍለ ከተማና የቀበሌ አደረጃጀት አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የሀዋሳ ከተማን የክፍለ ከተማና የቀበሌ አደረጃጀት እንዲሁም የቀበሌ መንግሥታዊ ተቋማት አወቃቀርን አፀደቀ።

በዚህም መሠረት የሀዋሳ ከተማ በ3 ክፍለ ከተማና እያንዳንዱ ክፍለ ከተማ በ3 ቀበሌዎች እንዲደራጅ ምርክ ቤቱ አጽድቋል።

እንዲሁም የቱላ ክፍለ ከተማ 2 የከተማ ቀበሌዎችንና 9 የገጠር ቀበሌዎችን ይዞ ቀድሞ በነበረበት አወቃቀር እንዲቆይ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብም ምክር ቤቱ ተቀብሎ አጽድቋል።

በቱላ ክፍለ ከተማ ስር የተዋቀሩት ሁለቱ የከተማ ቀበሌዎች የራሳቸው ስኬች ፕላን እንደሚኖራቸውም ተመልክቷል።

የቀበሌ አከላለልና ስያሜን በተመለከተም የአገልግሎት ተደራሽነትና ምቹነትን መሠረት ባደረገ መልኩ የክልሉ የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ከከተማ አስተዳደሩና ከህዝቡ ጋር በመወያየት መስፈርቱን ሳያጓድል እንዲፈጽም ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል።

በተያያዘ ምክር ቤቱ የክልሉ የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ የደረጃ ለውጥ እንዲደረግላቸው ካቀረባቸው 13 ከተሞች መካከል መስፈርቱን ያሟሉ የ9 ከተሞችን ጥናት አጽድቋል።

በጥናቱ መሠረት መስፈርቱን አሟልተው የፈርጅ 3 ደረጃ የፀደቀላቸው ወንዶ ገነት፣ አለታ ጩኮ፣ ካራት፣ ጉኑኖ ሐሙስ፣ ጊንቢቹ፣ ገደብ፣ ገሱባ፣ ጃጁራና ጨለለቅቱ ከተሞች መሆናቸው ታውቋል።

ሌሎች መስፈርቱን ያላሟሉ ከተሞች ጥናት ተጨማሪ ጊዜ ተወስዶ እንዲታይ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ሌሎች ከተሞችን እንደዚሁ የከተማ ባህሪ የሚታይባቸውንና በከተማ ሊካለሉ የሚችሉትን የመደገፍና በጥናት በመለየት የማቅረብ ስራውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ምክር ቤቱ አመልክቷል።

መረጃውን ከደቡብ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ነው ያገኘነው።