የቅማንት ብሄረሰብ የራስ አስተዳደርን የማዋቀር ስራ በቅርቡ ይጀመራል-አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቅማንት ብሄረሰብ የራስ አስተዳደር ምስረታ ቅድመ ዝግጅት በአብዛኛው በመጠናቀቁ አስተዳደሩን የማዋቀር ስራ በቅርቡ እንደሚጀመር የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አስታወቁ፡፡

አስተዳደሩን ለመመስረት በሚቻልበት ዙሪያ በጎንደር ከተማ ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ የምክክር ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል።

በጉባዔው ላይ የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንደተናገሩት፥ የቅማንት የራስ አስተዳደር መቋቋሙ ለክልሉ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው።

"የክልሉ መንግስት በየደረጃው ስምምነት በተደረሰባቸው ቀበሌዎች የቅማንት የራስ አስተዳደር ምክር ቤቶች እንዲቋቋሙ በማድረግ የአካባቢው ልማትና መደበኛ የመንግስት የስራ እንቅስቃሴ እንዲጠናከር አመቺ ሁኔታዎችን ይፈጥራል” ብለዋል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ የቅማንት ብሄረሰብ የማቋቋሚያ አዋጅ በክልሉ ምክር ቤት እንዲሻሻል በማድረግ የቀበሌም ሆነ የወረዳ ምክር ቤቶች በይፋ ተመስርተው የህዝቡን የዘመናት ጥያቄ መቋጫ እንደሚያገኝ ገልጸዋል።

"በአስተዳደራዊ አወቀቃቀር ኩታ ገጠም ያልሆኑ ቀበሌዎችንና ጎጦችን በማካለሉ ስራ በመተማ ወረዳ የሶስት ቀበሌዎችን አከላለል በተመለከተም ህገ መንግስቱን መሰረት ያደረገ ምላሽ የሚያገኙበት ሁኔታ ይመቻቻል" ብለዋል፡፡

በአከላለል ሂደቱ ስምምነት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ አግባብ በየደረጃው ላለ አካል ጥያቄ ማቅረብ እንደሚቻልም ርሰስ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

የቅማንት ብሄረሰብ የአስተዳደር ምስረታ መጓተት የአካባቢውን ህብረተሰብ የልማቱ ተጠቃሚ ማድረግ እንዳልተቻለ ያመለከቱት አቶ ገዱ፥ ለአስተዳደሩ ምስረታ የአማራም ሆነ የቅማንት ተወላጆች ተገቢውን ድጋፍ እንዲሰጡ አሳስበዋል።

የቅማንት ብሄረሰብ የራስ አስተዳደር ምስረታ ቅድመ ዝግጅት በአብዛኛው በመጠናቀቁ የማዋቀር ስራ በቅርቡ እንደሚጀመር ነው ያስታወቁት።

kemant2.jpg

የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ያለው አባተ በበኩላቸው፥ የቅማንት አስተዳደርን ለመመስረት በጥምር ኮሚቴው የተከናወኑ ቅድመ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ከቀረበው ሪፖርት መገንዘብ እንደቻሉ ተናግረዋል።

በአስተዳደራዊ አከላለሉ ሂደት ስምምነት ያልተደረሰባቸው የመተማ ወረዳ ሶስት ቀበሌዎች የህግ ትርጉም እንዲሰጣቸው በፌደሬሽን ምክር ቤት በኩል ሊቀርቡ እንደሚችል ጠቁመዋል።

የቀበሌዎቹ የአከላለል ሂደት የብሄረሰቡን አስተዳደር ከመመስረት የሚያግደው ባለመሆኑ የህዝቡ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በአፋጣኝ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

"የቅማንት አስተዳደር ምስረታ ቅድመ ዝግጅቱ በአብዛኛው ወሳኝ በሆነ ሁኔታ የተጠናቀቀና ጥምር ኮሚቴውም የተሻለ ተግባር ፈጽሟል" ያሉት ደግሞ የፌደራል እና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ናቸው፡፡

በአስተዳደራዊ የማካለል ሂደቱ የተከሰቱ አለመግባባቶች የማንኛውንም ወገን መብቶች ሳይጥስ በህዝባዊ ምክክርና በውይይት ሊፈቱ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የቅማንት ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ሰማልኝ ዘገየ በበኩላቸው የቅማንት አስተዳደርን ለመመስረት እየተደረገ ባለው ጥረት የሚስተዋሉ አደናቃፊ ጉዳዮች በህግ አግባብ ሊፈቱ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በቆየው የቅማንት አስተዳደር ምስረታ የምክክር ጉባኤ ላይ ከማዕከላዊና ከምዕራብ ጎንደር ዞኖች ከሚገኙ 110 ቀበሌዎች የተውጣጡ የቅማንትና የአማራ ተወላጆች ተሳትፈዋል።

 

ምንጭ፦ ኢዜአ