ኢትዮጵያ በዳርፉር ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ለሚደረገው ጥረት ድጋፏን እንደምትቀጥል አረጋገጠች

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ በዳርፉር ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የሱዳን መንግስት እያደረገ ላለው ጥረት ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተቀዳ አለሙ ተናግረዋል።

አምባሳደር ተቀዳ ይህን ያሉት በድርጅቱ የዳርፉር ተልእኮ ጉዳይ ላይ ትኩረት በማድረግ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሃፊ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ውይይት በተደረገበት ወቅት ነው።

በአካባቢው ያለው የሰላም ሁኔታ መሻሻል እያሳየ መሆኑን ያነሱት ቋሚ መልዕክተኛው፥ የሱዳን መንግስት እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦም እንደሚበረታታ ነው የገለፁት።

አሁን ላይ እየተካሄደ ያለው ትጥቅ የማስፈታት ሂደት በአካባቢው የሚስተዋለውን ተደጋጋሚ ግጭት እንደሚያስቀር እና የዳርፉርን ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ምቹ ሁኔታ መሆኑን ተናግረው ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ነው የጠየቁት።

ይህን ማድረጉ ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ መጡበት አካባቢ ለመመለስ ያስችላል ያሉት አምባሳደር ተቀዳ፣ የሀገሪቱ መንግስት ለሚያደርገው ጥረት የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የሱዳን መንግስት በቀጠናው ያለውን አለመረጋጋት ተቋቁሞ የሰላም ስምምነቱን ለመተግበር እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች የሚበረታቱ እንደሆኑም አምባሳደሩ ገልጸዋል።

በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ሁሉም ታጣቂ ሃይሎች ከጥቂት ዓመታት በፊት በዶሃ/ኳታር ለተፈረመው የዳርፉር የሰላም ስምምነት ትግበራ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተገዥ እንዲሆኑ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

ለሰላም ሂደቱ ጥረት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የፋይናንስና የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀጥልም አምባሳደር ተቀዳ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በምዕራብ አፍሪካ፣ በሳህል እና በቻድ አካባቢ ያሉ ባለ ብዙ ገፅታ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የዓለም አቀፍ እና ቀጠናዊ ወገኖች ዘላቂ ትብብርና አጋርነት ወሳኝ መሆኑን ኢትዮጵያ ትኩረት እንደምትሰጠው ነው አምባሳደር ተቀዳ የተናገሩት።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው ስብሰባ በድርጅቱ የምዕራብ አፍሪካ እና የሳህል አካባቢ እንዲሁም የቻድ ሃይቅ ተልዕኮን የስድስት ወር ሪፖርትን መገምገሙን ኢዜአ ዘግቧል።