ዩክሬን ከ20 ሺህ በላይ ተጨማሪ ሰላም አስከባሪ እንደሚያስፈልጋት ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዩክሬን ካለችበት ቀውስ ለመውጣት ተጨማሪ ከ20 ሺህ በላይ ሰላም አስከባሪ እንደሚያስፈልጋት ተገለፀ።

ከዚህ ውስጥ አብዛኛውን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ካልሆኑ ሀገራት ሊዋጣ እንደሚገባም ነው የተጠቆመው።

ይህ እቅድ የተዘጋጀው በቀድሞ የኔቶ ዋና ጸሀፊ እና በዩክሬኑ ፕሬዚዳንት አማካሪ አንድሬ ፎግ ራስሙሰን ሲሆን፥ በቀናት ውስጥም ለመንግስታቱ ድርጅት ይቀርባል ተብሏል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2014 ጀምሮ ዩክሬን በገባችበት አለመረጋጋት ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይህን እስከ ጭራሹ ለማስቆምም ተጨማሪ ሀይል ያስፈልጋል ተብሏል።

ሩስያ በምስራቅ ዩክሬን በሚሰፍሩ የምእራባውያን ሀገራት ወታደሮች ላይ ቅሬታዋን እያሰማች ነው።

ምንጭ፦ www.reuters.com