አይ ኤስ በኢራቅ መንግስት የሚደገፉ 25 ታጣቂዎችን መግደሉ ተነገረ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 12 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) አይ ኤስ በኢራቅ ኪርኩክ ግዛት በከፈተው ጥቃት በመንግስት የሚደገፉ 25 ታጣቂዎች መግደሉን የሃገሪቱ ፖሊስና ወታደራዊ አዛዦቸ ተናገሩ።

ወታደራዊ አዛዦቹ ቀደም ብለው 12 ታጣቂዎች መገደላቸውንና ሌሎች 10 ወታደሮች የገቡበት እንዳልታወቀ ገልጸው ነበር።

ይሁን እንጅ የሌሎች 13 ታጣቂዎች አስከሬን ዘግየት ብሎ በመገኘቱ የሟቾቹ ቁጥር 25 መድረሱ ተገልጿል።

ጥቃት አድራሹ አይ ኤስ የፖሊስ ዩኒፎርም በመጠቀም ሌሎች ጥቃቶችን እንዳያደርስ የፀጥታ አካላት ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኙም ተነግሯል።

የኢራቅ ጦር ወሳኝ የነዳጅ ማስተላለፊያ በሚላት ኪርኩክ አካባቢ የሚገኘውን ተራራማ ስፍራ ከአይ ኤስ ለመቆጣጠር በዚህ ወር የተጠናከረ ዘመቻ መጀመሩ ይታወሳል።

በዚህ ተራራማ አካባቢ ሁለት ታጣቂ ቡድኖች ከመንግስት ጋር በመዋጋት ላይ ይገኛሉ።

ባግዳድ ባለፈው ታህሳስ ወር በአይ ኤስ ላይ ድል መቀዳጀቷን ማወጇም አይዘነጋም።

 

 

ምንጭ፦ ሬውተርስ