ኮለኔል ደመቀ ዘውዴን ጨምሮ ክሳቸው የተቋረጠላቸው ተጠርጣሪዎችና ፍርደኞች ተለቀቁ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሽብር እና በሁከት ወንጀል ተጠርጥረው በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን ሲከታተሉ የነበሩት ኮለኔል ደመቀ ዘውዴን ጨምሮ ሌሎች ክሳቸው እንዲቋረጥና ይቅርታ እንዲደረግላቸው በተወሰነው መሰረት ዛሬ ከማረሚያ ቤት ተለቀዋል።

ከኮለኔል ደመቀ በተጨማሪ በማረሚያ ቤት የነበሩ 16 ፍርደኞችም ይቅርታ የተደረገላቸው ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ አስሩ ዛሬ ተለቀዋል።

በዛሬው እለት ከጎንደር ማረሚያ ቤት የተለቀቁት ኮለኔል ደመቀ ዘውዴ በሰጡት አስተያየት፥ በማረሚያ ቤት በነበሩበት ጊዜ ለነበረው አያያዝ፣ የፍትህ ሂደት እና ህብረተሰቡ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ማንኛውንም ጥያቄ ህገ መንግስቱን በጠበቀ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲያቀርብም ጥሪ አቅርበዋል።

ኮለኔል ደመቀ በጥያቄ ሰበብ አድማ ማድረግ እና የሰው ህይወት መጥፋትንም አውግዘዋል።

ሌሎች ክሳቸው ተቋርጦ እና በይቅርታ የተለቀቁ ተጠርጣሪዎች እና ፍርደኞችም፥ ህብረተሰቡን ከተቀላቀሉ በኋላ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ህይወታቸውን እንደሚመሩ ገልፀዋል።

የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ የጎንደር ምድብ አስተባባሪ አቶ ብስራት አበራ፥ የድሮው አወቃቀር በሰሜን ጎንደር ዞን የተለያዩ ወንጀሎች ክስ የተመሰረተባቸው 254 ተከሳሾች ክስ እንዲቋረጥ እና 55 ፍርደኞች በይቅርታ እንዲፈቱ መወሰኑን አስታውሰዋል።

 

 

 

 

 

በምንይችል አዘዘው