የአውሮፓ ፓርላማ ተመድ በምስራቃዊ ጉታ ያስተላለፈው የተኩስ አቁም ውሳኔ እንዲተገበር ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዚዳንት በሶሪያ ምስራቃዊ ጉታ ላይ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የወሰነው የተኩስ አቁም ውሳኔ እንዲተገበር ጥሪ አቀረቡ።

የፓርላማው ፕሬዚዳንት አንቶኒዮ ታጃኒ በሰሜን የፈረንሳይ ግዛት በተካሄደው የአውሮፓ ፓርላማ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ እንደገለፁት፥ በምስራቃዊ ጉታ እያጋጠመ ካለው የንፁሃን ዜጎች ህይወት መጥፋትና የዘር ማጥፋት ማንም ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም።

በዚህም ታጃኒ በአውሮፓ ፓርላማ ስም በደማስቆ ከተማ ዳርቻ ላይ እየታየ ያለው አሳዛኝ ክስተት ለማቋረጥ የተኩስ አቁም ውሳኔው ተግባራዊ እንዲሆን ጠይቀዋል።

በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ባለፈው ወር መጨረሻ በሶርያ ውስጥ በተለይም ምስራቃዊው ጉታ አካባቢ ለ30 ቀናት የሚቆይ አስቸኳይ የተኩስ አቁም በማድረግ የሰብዓዊ እርዳታዎችን ለመስጠት እንዲፈቀድ የሚያስችል ውሳኔው በሙሉ ድምፅ አፅድቀዋል።

ይሁን እንጂ የሶርያ መንግስት እና ተባባሪዎቹ የፀጥታው ምክር ቤት በሶሪያ ያስተላለፈው ውሳኔ እስካሁን ተፈጻሚ አላደረጉትም።

ስለሆነም የፓርላማው ፕሬዚዳንት "ዘለቄታዊ የሆነ የተኩስ አቁም በማድረግ የአከባቢው ሰለማዊ ነዋሪዎች ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል” ብለዋል።

ለዚህም ነዋሪዎቹ ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ሁሉም ነገር በጄኔቫ ላይ በተደረገው ውሳኔ መከናወን አለበት ነው ያሉት።

ፕሬዚዳንት በሽር አላሳድ ባለፉት አምስት ዓመታት በምስራቃዊ ጎታ በሚፈፅሙት ጥቃት በርካቶች ሲሞቱ ወደ 400 ሺህ የሚያህሉ ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈላቅለዋል።

 

 

 

ምንጭ፦ aa.com.tr