የጋራ ምክር ቤቱ የሀገሪቷን ችግሮች ለመፍታት ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እንደሚሰራ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሀገሪቷን ወቅታዊ ችግሮች ለመፍታት ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራ አስታወቀ።

የጋራ ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው በሀገሪቷ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መክሯል።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቷ ለተፈጠረው ችግር መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በዘላቂነት ለመፍታት ብሔራዊ መግባባት የመፍጠር ስራ መከናወን እንዳለበት ነው የገለጸው።

ሁሉም የጋራ ምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎችም ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ የሚስተዋለውን ሀገራዊ ችግር መንስኤ በመመርመር መፍትሄ ማምጣት ያስፈልጋል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የተፈጠረውን ወቅታዊ ችግር የውጭ አካላት ጣልቃ ገብነት ሳይኖር ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ለመፍታት መመካከር የሚያስችል መድረክ እንደሚያስፈልግም የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።

የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ትግስቱ አወሉ፥ “መፍትሔው ብለን የምናስበው ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ብሔራዊ መግባባትን መቀበል ነው፤” ብለለዋል።

የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (ኢዴአን) ሊቀመንበር አቶ ጉዕሽ ገብረስላሴ በበኩላቸው፥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደ መፍትሔ ሳይሆን ለማረጋጋት እንደሚጠቅም ገልፀዋል።

የኢህአዴግ ተወካይ አቶ ሚሊዮን አብርሃ፥“ብሔራዊ መግባባት ሊሰራ የሚችል በኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን እዚህ ካለው ጀምሮ በጋራ የተወሰነ ሃሳብ የጋራ አድርጎ መውሰድ ነው” ብለዋል።

ለዚህም ብሔራዊ መግባባት ኢህአዴግ ያምንበታል ያሉት ኣቶ ሚሊዮን፥ “ይሄን ለማድረግ ግን የሁላችንም ተሳትፎ ነው የሚሆነው” ነው ያሉት።

በተያያዘ ዜና የጋራ ምክር ቤቱ በዛሬ ውይይቱ የኢትዮጵያ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢሰዴፓ/ን ቅሬታ የአጣሪ ኮሚቴው ባቀረበው ሪፖርት ላይ ተመስርቶ ለሁለተኛ ጊዜ ተወያይቶበታል።

“ፓርቲው የፖለቲካ ጫና ደርሶብኛል በሚል የግለሰብ ጉዳይ ወደጋራ ምክር ቤቱ በማምጣቱና በተደጋጋሚ የምክር ቤቱን አሰራርና ደንብ በመጣሱ ይቅርታ ይጠይቅ እና መቀጣት አለበት” በሚሉ ሃሳቦች ላይም ተከራክሯል።

ፓርቲው ይቅርታ እንደማይጠይቅ ሲያስታውቅ፥ 11 ፓርቲዎች “ከጋራ ምክር ቤቱ ለ6 ወራት ይታገድ” አንድ ፓርቲ ደግሞ “የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠው” የሚል አቋም በመያዝ ወጥተዋል።

 

 

 

ምንጭ፥ ኢዜአ