ሶሪያ በአሜሪካና አጋሮቿ ከተወነጨፈባት ሚሳኤል ከ71 በላይ የሚሆኑትን ማክሸፏን አስታወቀች

አዲስ አበባ ሚያዚያ 06፣ 2010፣ (ኤፍ.ቢ.ሲ) አሜሪካ እና አጋሮቿ ወደ ሶሪያ ካስወነጨፉት ሚሳኤል ከ71 በላይ የሚሆነው በሶሪያ አየር ሀይል እንደከሸፈ ደማስቆ እየተናገረች ነው።

የሶሪያ መንግስትን ኢላማ ያደረጉ ቶማሀውክስ ጨምሮ 103 ሚሳኤሎች አሜሪካ እና አጋሮቿ እንዳስወነጨፉ ተነግሯል።

በዚህ ጥቃት ወደ አል ዱማይር ወታደራዊ አውሮፕላን ማረፊያ 12 ሚሳዔሎች ተወንጭፈው እንደከሸፉ ታውቋል።

ሩሲያ እንዳስታወቀችው አሜሪካ አንድ ወታደራዊ መርከብ፣ ቢ 1 ቦንብ ጣይ አውሮፕላን ስትጠቀም ብሪታንያ በበኩሏ ቶሮኔዶ ተዋጊ ጀትን በዚህ ጥቃት አሳትፋለች።

ፈረንሳይም በዚህ ጥቃት ሚራጅና ራፋየል የተሰኙ የጦር ጀቶችን በመጠቀም 12 ሚሳዔሎችን እንዳስወነጨፈች እና ዒላማቸውን እንደመቱ አስታውቃለች።

ፕሬዚዳንት ትራምፕም በሶሪያ ላይ የተወሰደው የሚሳዔል ጥቃት ስኬታማ እንደሆነ ማዋጃቸው ተነግሯል።

ሩሲያም ይህን የሚሳዔል ጥቃት የሀገር ሉዓላዊነትና የተባበሩት መንግስታት ቻርተርን የጣሰ እርምጃ እንደሆነ በመግለፅ ተቃውማለች።

የሶሪያው ፕሬዚዳንት በሽር አላሳድ በበኩላቸው የፀጥታው ምክር ቤት የአሜሪካ እና አጋሮቿን ጠብጫሪ እርምጃ በተመለከተ ውይይት እንዲያካሂድ ጥሪ አቅርበዋል።

ምንጭ፦ አልጅዚራ እና ሲ ኤን ኤን

ተተርጉሞ የተጫነው፦ በኤፍሬም ምትኩ