የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ለ150 የጎዳና ተዳዳሪዎች ነፃ የሕክምና አገልግሎት ሰጠ

አዲስአበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2010 (ኤፍቢሲ) የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ከአራዳ ኬር ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በመዲናዋ ለሚገኙ 150 የጎዳና ተዳዳሪዎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ፡፡

ሆስፒታሉ ለጎዳና ተዳዳሪዎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው ተብሏል።

ሆስፒታሉ ተከታታይ ህክምና ማግኘት የሚያስችላቸውን ስርዓት በመዘርጋት ካሉባቸው የጤና ችግሮች እንዲፈወሱ ሙሉ የህክምና አገልግሎት እየሰጣቸው መሆኑንም ዶክተር ሰለሞን ደሳለኝ ገልጸዋል።

የአራዳ ኬር ፋውንዴሽን መስራች አቶ ሄኖክ ዓብይ ነጻ ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን በርካታ የጎዳና ተዳዳሪዎች ለመደገፍ በማሰብ ከአራት ዓመታት በፊት ማሕበሩን መመስረታቸውን ገልጸዋል።

ፋውንዴሽኑከዚህ ቀደም ለጎዳና ተዳዳዎቹ የምገባና የአልባሳት ድጋፍ ሲያደርግ እንደቆየም ተነስቷል፡፡

እንዲሁም ከሆስፒታሉ ጋር በመተባበር ሕክምና እንዲያገኙ ሲያደርግ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የሕክምና ፕሮግራሙ አስተባባሪ ወይዘሮ ቅድስት ተስፋዬ በእስካሁን ሂደት የቆዳና የጉበት በሽታዎች በአብዛኞቹ የጎዳና ተዳዳሪዎች ላይ የሚስተዋሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም ከመንግስት ጋር በመስራት መማር የሚፈልጉ እንዲማሩ መስራት የሚሹም እንዲሰሩ ይደረጋል ብለዋል።

የጎዳና ተዳዳሪዎችም የተደረገላቸው ሕክምና በቀጣይ የተስተካከለ ሕይወት እንዲኖሩ ተስፋ እንደሰጣቸው ገልጸው፥ ዕድሉን ያላገኙትም ህክምና የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።


ምንጭ፦ኢዜአ