የደብረታቦር - ጃራገንዶ 88 ኪሎ ሜትር የአስፖልት መንገድ ግንባታ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 8 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባውና 88 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የደብረታቦር - ጅብ አስራ ማርያም - ጃራገንዶ የአስፓልት መንገድ ግንባታ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

በባለስልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ፥ መንገዱ የንኮማንድ በተባለ ሃገር አቀፍ ተቋራጭ እንደተሰራና ሙሉ ወጭው በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ መሆኑን ገልጸዋል።

በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ማጠናቀቂያ ላይ አጠቃላይ የሃገሪቱ የመንገድ አውታር 110 ሺህ ኪሎ ሜትር እንደነበር ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የመንገድ አውታሩን 210 ሺህ ኪሎ ሜትር ለማድረስ ታስቦ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ግቡን ለማሳካትም መንግስት በርካታ የአዳዲስ መንገዶች ግንባታና የደረጃ ማሻሻል ስራዎች እያከናወነ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው መንገዱ በእግር ጉዞ ከስድስት ሰዓት በላይ ያደርጉት የነበረውን ጉዞ፥ ወደ አንድ ሰዓት ዝቅ በማድረግ እንግልት እንደቀነሰላቸው ተናግረዋል።

አሁን ላይ በፌደራል መንገዶች ግንባታ የተሰማሩ 100 የሚሆኑ የሃገር ውስጥ ተቋራጮች እንደሚገኙ ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ከደብረታቦር - ጅብ አስራ ማርያም - ጃራገንዶ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የማጠናቀቂያ ስራ ትናንት በባለሙያዎች መጎብኘቱን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።