በደቡብ ክልል ቤት የመስራት አቅም ለሌላቸው ነዋሪዎች የኪራይ ቤት ግንባታ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 8 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ቤት የመስራት አቅም ለሌላቸው ነዋሪዎች በኪራይ የሚሰጥ የቤት ግንባታ እያከናወነ መሆኑን የክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ይናገራሉ።

ከዚህ ባለፈም የቤት ቁጥርና የፈላጊዎች ቁጥር አለመጣጣምም ሌላው ችግር መሆኑንም ነው የሚናገሩት።

ሁኔታው አሳሳቢ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም መንግስት በጉዳዩ ላይ ሊያስብበት እንደሚገባ ይናገራሉ።

የክልል መዲና በሆነችው ሃዋሳም የቤት እጥረትና የኪራይ ቤት ውድነት እንደሚስተዋል ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የክልሉ ከተማ ልማት እና ቤቶች ቢሮም ይህን ችግር ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ክፍሌ ገብረማርያም በተያዘው አመት ቁጠባ በመቆጠብ የማህበር ቤት ለሚሰሩት መሬት፥ እንዲሁም በኪራይ ለሚፈልጉ

የመንግስት ሰራተኞችና ነዋሪዎች ደግሞ በኪራይ የሚሰጥ የቤት ግንባታ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በዚህም መሰረት ተደራጅተን በመቆጠብ ቤት እንሰራለን ብለው ጥያቄ ላቀረቡና 4 ሚሊየን 433 ሺህ 640 ብር ለቆጠቡ፥ ከ1 ሺህ 300 በላይ ነዋሪዎች 3 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት መቅረቡንም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ 10 በመቶ ለቆጠቡ መምህራን የማህበር ቤት ግንባታ ማከናወኛ መሬት መሰጠቱንም ነው የተናገሩት።

በኪራይ ለሚፈልጉ የመንግስት ሰራተኞችና ነዋሪዎች ደግሞ በክልሉ አራት ከተሞች ከ11 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የ406 ቤቶች እየተገነቡ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥ የ156 ቤቶች ግንባታ በሃዋሳ ከተማ እየተከናወነ ሲሆን፥ በኪራይ የሚተላለፉ ቀሪ 250 ቤቶች ግንባታ ዲዛይን መጠናቀቁንም ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈም የክልሉ መንግስት አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ቤት ለመገንባት በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የመስሪያ ቦታ ለይቷል ነው ያሉት።

እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎችም መኖሪያ ቤቱ በሚገነባላቸው አካባቢ እየኖሩ በተለያየ የስራ ፈጠራ ተሰማርተው ህይወታቸውን እንዲመሩ ይደረጋል።

 

በታሪክ አዱኛ