ጨፌ ኦሮሚያ ከ63 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ሆኖ የቀረበለትን የ2011 የክልሉን በጀት አፀደቀ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 4 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ጨፌ ኦሮሚያ ከ63 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ሆኖ የቀረበለትን የ2011 የኦሮሚያ ክልል መንግስት በጀት አፀደቀ።

የጨፌ ኦሮሚያ 8ኛ መደበኛ ጉባኤ የክልሉን መንግስት የ2011 በጀት እና ረቂቅ አዋጅን በማጽደቅ አጠናቋል።

በዛሬው ውሎው 63 ቢሊየን 440 ሚሊየን 979 ሺህ 580 ብር ሆኖ የቀረበለትን የ2011 የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በጀትን አጽድቆታል።

ከበጀቱ ውስጥ ከ12 ነጥብ 2 ቢሊየን በላይ ብሩ ለተዘዋዋሪ ፈንድ የሚውል ይሆናል።

ከ14 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ደግሞ ለካፒታል በጀት የተመደበ ነው።

36 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ደግሞ ለወረዳና ከተሞች ድጋፍ የሚውል ሲሆን፥ 500 ሚሊየን ብር ተጠባባቂ በጀት እንዲሆን አጽድቆታል።

በተጨማሪም የክልሉን ኦዲት ቢሮ የ2011 በጀት እቅድ እና የጨፌ ኦሮሚያ ፅህፈት ቤት ሪፖርትን አድምጦ ከተወያየ በኋላ አፅድቆታል።

ጨፌው በተያዘው አመት ሊካሄድ የነበረው የወረዳ፣ ከተማ እና የቀበሌ ምርጫም ካለው ሁኔታ አንጻር አመች ባለመሆኑና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ እንዲያስችል በቀጣዩ አመት እንዲካሄድም ወስኗል።

ከዚህ ባለፈም በተለያየ ምክንያት መስራት ያልቻሉ የቋሚ ኮሚቴ አባላትን የሚተኩ ሰዎችንም ሾሟል።

በሰርካለም ጌታቸው