ኬንያ የተዘረፈ ሐብቷን ለማስመለስ ከስዊዘርላንድ መንግስት ጋር ተስማማች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የስዊዘርላንድ አቻቸው ኤሊየን ቤሴይት ከኬንያ ተዘርፎ በስዊዝ ባንክ የሚገኝ ሐብት ለማስመለስ መፈራረማቸው ተገለጸ፡፡

ሁለቱ ሀገራት ስምምነቱን ያጸደቁት የስዊዘርላንድ ፕሬዚዳንት ለሁለት ቀናት የቆየ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በኬንያ ባደረጉበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡

ኬንያ ወደ ሀገራ ለማስመለስ ያቀደችው ገንዘብ ከዚህ ቀደም በሙስና የሸሸ መሆኑንም ገልጻለች፡፡

ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ከሁለተኛው ዘመን የምርጫ ቅስቀሳቸው ጀምሮ የሀገሪቱን የወደፊት ዕጣ ፈንጣ እየተፈታተነ ነው ያሉትን ሙስና ለመዋጋት ቆርጠው መነሳታቸው ተነግሮዋል፡፡

የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከስዊዘርላንድ መንግስት ጋር ስምምነት በመድረስ በሙስና የተመዘበረ ሃብት ወደ ሃገር እያስመለሱ ይገኛሉ ከነዚህም መካከል ናይጄሪያ በሳኒ አባቻ የተዘረፈ ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ እንደተመለሰላት ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ማናጋጓዋም በተመሳሳይ መንገድ ከሀገራቸው የሸሸ ሐብት ማስመለሳቸው ተነግሮዋል፡፡

በሙስናና ህጋዊ ባልሆኑ መንገዶች አማካኝነት ከአፍሪካ በየዓመቱ 150 ቢሊየን ዶላር እንደሚሸሽ የተባበሩት መንግስታት የኢኮኖሚ ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል፡፡

 


ምንጭ፦ ካፒታልኤፍኤም
በአብርሃም ፈቀደ