የጠቅላይ ሚኒስትሩ የ100 ቀናት ቆይታ ከዲፕሎማሲው አንጻር

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኃላፊነት ከተረከቡ 100 ቀናት ጊዜ ውስጥ የላቀ የውጭ ግንኙነት እና የዲፕሎማሲ ስራ መከናወኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደ ተቋም የተጋጋለ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ስራ መከናወኑ አንስቷል፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ዛሬ በአንድ መቶ ቀናት አንድ ሺህ አንድ ስኬት በሚል ርዕስ ዶክተር አብይ በአጭር ጊዜ ብዙ የዲፕሎማሲ ስኬት ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ያለማንም ሦስተኛ አካል ጣልቃ ገብነት የአስመራ ዲክላሪሽን ወይም የጋራ መግለጫ ተፈርሟል ብለዋል። 

ስምምነቱ ሰላም እና ፍቅር ጥላቻን ያሸነፉበት እንደሆነም ተናግረዋል።

የሁለቱ ሀገር መሪዎች ይህንን በማድረጋቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢጋድ የአፍሪካ ህብረት፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሀገሮች በተናጠል ድጋፋቸውን እየገለፁ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ገልፀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የብሄራዊ ጥቅም እና ብሄራዊ ደህንነት የሚያረጋግጡ ውጤቶች መመዝገቡን አንስተው፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር በተለይም በጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ግብፅ፣ ዮጋንዳ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ እንዲሁም የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኤምር በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው የተለያዩ ውጤቶች መመዝገቡን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አዲስ አበባ ውስጥ ላለው የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱት ችግሮች በራሳችን አቅም እየተፈቱ መሆኑን የማስረዳት ስራ ማናወኑን ገልጸዋል፡፡

በባለ ብዙ መድረኮች በአፍሪካ ህብረት፣ በኢጋድ እንዲሁም የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ተለዋጭ አባል በመሆኗ በዓለም አቀፍ መድረኮች የዲፕሎማሲ ሚና ከፍ ብሎ እንዲታይ ለማድረግ መቻሉንም አቶ መለስ ተናግረዋል።

በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መስኩ ባለሃብቶችን የመሳብ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉ የተጠቀሰ ሲሆን፥ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና የሳዑዲ አረብያ ባለሃብቶች፣ አይቢኤም ዩፒኤስ ጀነራል ሞተርስ የመሳሰሉ 36 የአሜሪካ ኩባንያዎች እንዲሁም ከእስያ ሀገሮች በተለይም ከቻይና እና ከህንድ የመጡ ኩባንያዎች የቅድመ ኢንቨስትመንት ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

ባለፉት 100 ቀናት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የዜጋ ዲፕሎማሲ መሰራቱን አንስተው፥ መንግስት ባለፈው አንድ ዓመት ባደረገው ጥረት 3000 ያህል ኢትዮጵያውያንን ከሳዑዲ አረብያ፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ እና ሱዳን በማስፈታት ለሀገራቸው አብቅቷል፡፡

ኢትዮጵያ ካላት ተደማጭነት የዲፕሎማሲ እና የኢኮኖሚ አቅም ጋር ያላትን ውክልና ለማስፋት በአውሮፓ ዘሄግ ኒዘርላንድ፣ በአፍሪካ ታንዛንያ ዳሬሰላም የቆንስላ ጽህፈት ቤቶች እና ኤምባሲ ተከፍቷል፡፡

ወደሀገራቸው የሚመለሱ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ቁጥር መጨመሩን እንዲሁም ለረጅም ዓመታት በሌሎች ሀገራት ሲኖሩ የነበሩ የፖለቲካ ቡድኖች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ዜጎቻችንን ለማነጋገር ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን አቶ መለስ አስታውሰዋል፡፡