በትግራይ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች በጥቂት ስደተኞች የተካሄደውን ረብሻ አወገዙ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 18፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትግራይ ክልል የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ባለፈው መስከረም 25 እና 27  በጥቂት ስደተኞች የተፈጠረው ረብሻ እንደማይወክላቸው ገለፁ።

በማይ አይኒ፣ አዲ ሀሩሽና ሽመልባ የሚገኙ ስደተኞች ናቸው ረብሻውን የፈጠሩት ጥቂት ግለሰቦች አይወክሉንም ሲሉ  ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ ያካሄዱት።

የሻዕቢያ እጅ እንዳለበት የተገመተው ይህ ሁከትም ኢትዮጵያ ለስደተኞች የምትመች አገር አይደለችም የሚለውን ምስል ለመፍጠር ታስቦ እንደተፈፀመም በዛሬው ሰልፍ ላይ የተካፈሉ ስደተኞች ተናግረዋል ።

በትግራይ ክልል በሚገኙ አራት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙት እነዚህ 25, 000 የሚጠጉ ስደተኞች ፥ በጥቂት ስደተኞች አቀናባሪነት ተፈፅሞ የነበረው ሁከት እንደማይወክላቸው በመግለጽ የኢትዮጵያን መንግስትና ህዝብ ይቅርታ ጠይቀዋል።

በተያያዘ ረብሻውን የፈጠሩት ግለሰቦችም ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝም ነው የተመለከተው ።

ስደተኞቹ በአብዛኛው ከ19 እስከ 35 ባለው የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሲሆ ፥ የኢትዮጵያ መንግስትም በርከት ላሉ ኤርትራዊያን ስደተኞች በአሜሪካ፣ ካናዳ እንዲሁም አውስትራሊያ መንግስት ድጋፍ የትምህርት እና የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል።

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከ425 ሺህ በላይ ስደተኞች ይገኛሉ።


በታደሰ ብዙዓለም

Comments

Name *
Submit Comment