ሌሎች አራት የሙስና ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታን ጨምሮ በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ቁጥር  54 ደርሷል።

ቁጥራቸው 54 የደረሰው ዛሬ በፌዴራሉ  ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት የጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው አራት ግለሰቦች በመካተታቸው ነው።   

በዚህም መሰረት የባለስልጣኑ የናዝሬት ቅርንጫፍ ሰራተኛ አቶ መልካሙ እንድሪስ ፣ የዋው ትራንዚት ስራ አስኪያጅ  ወይዘሮ አልማዝ ከበደ ፣ አቶ ዳዊት መኮንን እና አቶ ደጉ ሃቢቾ የተባሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ከህገ ወጥ ነጋዴዎች ፣ አስተላላፊዎች እና ጉዳይ አስፈጻሚዎች ጋር በመመሳጠር ፥ የኮንትሮባንድ እቃዎችን በናዝሬት በኩል ሳይፈተሹ ወደ አዲስ አበባ በማስገባት ፤ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች በህግ እንዳይጠየቁ በማድረግ እና ህገ ወጥ ጥቅም ማካበት በሚሉ የሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን የፌዴራል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ለተጨማሪ ምርመራ የጠየቀውን የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ 10 የምርመራ ቀናትን በመፍቀድ ለግንቦት 23 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

በተጨማሪ  የዋው ትራንዚት ስራ አስኪያጅ   ወይዘሮ አልማዝ ከበደ ከብርበራው ጋር በተያያዘ የታሸገ ቢሯቸው እንዲፈታ እና ፥ አቶ ዳዊት መኮንን የተያዘ መኪናቸው እንዲለቀቅላቸው በጠበቆቻቸው  አማካኝነት ጠይቀው ችሎቱ ጠበቆቻቸው አቤቱታቸውን በጽሁፍ እንዲጠይቁ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

በሌላ በኩል ችሎቱ የኬኬ ትሬዲንግ ባለቤት የሆኑት አቶ ከተማ ከበደ በብርበራ ወቅት ቢሯቸው እስካሁን በመታሸጉ ፥  የድርጅቶቻቸው ስራዎች መጎዳታቸውን በመጥቀሰ እሽጉ እንዲነሳላቸው ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፥ ለሃሙስ ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

 

በጥላሁን ካሳ

 


Comments

Name *
Submit Comment