Fana: At a Speed of Life!

ሃብታቸውን ያላስመዘገቡ 100 የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ሀብት እንዲጣራ ለፌደራል ፖሊስ ሊተላለፍ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል ሥነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ሀብትና ንብረታቸውን ያላስመዘገቡ 100 የፌደራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አስፈላጊው የህግ ማጣራት እንዲደረግባቸው ስም ዝርዝራቸውን ለፌደራል ፖሊስ እንደሚያስተላልፍ አስታወቀ።
 
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች 1 ሺህ ብር እየተቀጡ ሀብትና ንብረታቸውን እንዲያስመዘግቡ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ እስከ ዛሬ 11 ሰዓት ከ30 ድረስ ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል።
 
ይህንን አስመልክቶም በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ሀብትና ንብረታችውን ያላስመዘገቡ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የህግ ማጣራት እንዲደረግባቸው ለፌደራል ፖሊስ ስም ዝርዝራቸው ይተላለፋል ነው ያሉት።
 
ኮሚሽኑ ከተሰጡት ተልዕኮዎች አንዱ በፌደራል፣ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የመንግስት ተመራጮችና ተሿሚዎች ሀብትና ንብረታቸውን እንዲያስመዘግቡና እንዲያሳውቁ ማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል።
 
በዚህም በፌደራልና በአዲስ አበባ የሚገኙ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ሀብትና ንብረታቸውን እንዲያስመዘግቡ መገናኛ ብዙኀንን ጨምሮ በተለያዩ አማራጮች ጥሪ ቀርቦ እንደነበር አስታውሰዋል።
 
የተሰጠውን የጊዜ ገደብ ተጠቅመው ሀብትና ንብረታቸውን ያላስመዘገቡ 180 የሚሆኑ በፌደራልና አዲስ አበባ የሚገኙ የስራ ኃላፊዎች የተደረገውን ጥሪ ተቀብለው ባለማስመዝገባቸው እስከ ዛሬ ድረስ 1 ሺህ ብር የቅጣት መቀጮ ተጥሎባቸው ሀብትና ንብረታቸውን እንዲያስመዘግቡ ተደርጎ ነበር።
 
ከላይ ከተጠቀሱት 180 የስራ ኃላፊዎች ውስጥ 80 የሚሆኑ የስራ ኃላፊዎች እየተቀጡ ማስመዝገባቸውን ጠቁመዋል።
 
ቀሪዎች 100 የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ግን በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ባለማስመዝገባቸው አስፈላጊው የህግ ማጣራት እንዲደረግባቸው ለፌደራል ፖሊስ ስም ዝርዝራቸው እንደሚተላለፍ ገልጸው፤ በቀሩት ሰዓታት ውስጥ ሀብትና ንብረታቸውን እንዲያስመዘግቡም ጥሪ መቅረቡን ኢዜአ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.