Fana: At a Speed of Life!

ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሀገር ለማፍረስ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ መንግስት ህጋዊ እርምጃ ይወስዳል – የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 24 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሀገርን ለማፍረስ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ መንግስት ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ አጥፊዎችን ለፍትህ እንደሚያቀርብ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

በሃይማኖት ሽፋን ሀገርን የማፍረስ ሴራ ያነገቡ ኃይሎች በቅርቡ በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች አንዳንዴ ብሔርን ሌላ ጊዜ ደግሞ ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየሠሩ መሆኑን አስታውሰዋል።

“እኛ ኢትዮጵያዊያን የረጅም ጊዜ ታሪካችን የሚያሳየው ከወንድማማችነትና እህትማማችነት ውጪ ያለው መንገድ የጥፋት ነው” ያሉት አቶ አሻድሊ፣ በመሆኑም የብሔር፣ የኃይማኖት፣ የቋንቋ ብዝኃነት የሚስተናገድባትን ሀገር ወደእርስ በርስ ግጭት ለማስገባት የሚሠሩ አካላትን መንግስት አይታገስም ብለዋል።

መንግስት በቅርቡ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ በሃገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ግጭት ለመቀስቀስ እየሠሩ ባሉት አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ በቀጣይም ይህንኑ የህግ ማስከበር ተግባር አጠናክሮ ለማስቀጠል ከምንጊዜውም በላይ ቁርጠኛ መሆኑንም ርእሰ-መስተዳድሩ ገልጸዋል።

መላው የሃገራችን እና የክልላችን ህዝቦች ከመንግስት ጎን በመቆም ለዘመናት በአብሮነት የቆዩ ሕዝቦችን ወደግጭት ለማስገባት የሚሠሩ አካላትን አጋልጦ በመስጠትና በመጠቆም ለዘላቂ ሠላም መስፈን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አቶ አሻድሊ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይም ወጣቶች የሃይማኖት አባቶች የሚያስተምሯቸውን አስተምህሮዎች በአግባቡ መተግበር ይጠበቅባቸዋል ያሉት ርዕሰ-መስተዳድሩ፣ በስሜት በመገፋፋት የጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያ ከመሆን ራሳቸውን እንዲጠብቁም አሳስበዋል።

ርዕሰ-መስተዳድሩ ለመላው የእምልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1443ኛው የዒድ-አልፈጥረ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

መላው የሙስሊም ማኅበረሰብ በረመዳን ወር የተቸገሩትን በመርዳት እና ማዕድ በማጋራት ያሳየውን በጎ ተግባር በቀጣይም ለሃገር አንድነትና በሠላም ግንባታ የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.