Fana: At a Speed of Life!

ህብረተሰቡ የምርጫ ካርድ ከወዲሁ በመውስድ ሊዘጋጅ ይገባል – የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ህብረተሰቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን የሚያስጠብቅለትን ወኪል ለመምረጥ የሚያበቃውን የምርጫ ካርድ ከወዲሁ በመውሰድ ሊዘጋጅ እንደሚገባ የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ አሳሰቡ።

ርዕሰ-መስተዳድሩ በአውሲ-ረሱ ዞን ጭፍራ ወረዳ በመገኘት የመራጭነት ካርድ በወሰዱበት ወቅት እንደተናገሩት፤ 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግልጽ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግስት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየሰራ ነው።

ምርጫውን በስኬት ለማጠናቀቅ ጉዳዩ ለመንግስትና ምርጫ ቦርድ ብቻ የሚተው ሳይሆን ከህብረተሰቡ ጀምሮ የሁሉም አካላት ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይም በክልሉ የሚወዳደሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እስከታችኛው አስተዳደር እርከን ድረስ አባላቶቻቸውን አስተባብረው በመስራት የበኩላቸውን ሚና መጫወት እንደሚኖርባቸው ጠቅሰዋል።

በቀሩት ጥቂት ቀናት ህብረተሰቡ መብቱን የሚያስጠብቅለትን ወኪል ለመምረጥ የሚያበቃውን የምርጫ ካርድ በአቅራቢያው በተመቻቹ የምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት በመውሰድ ሊዘጋጅ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ህብረተሰቡ በወሰደው የምርጫ ካርድ በመጠቀም ለሀገርና ህዝብ የሚበጁ ወኪሎችን ለመምረጥ የፓርቲዎችን የምርጫ ፕሮግራም በተገቢው በመከታተል ውሳኔ ላይ መድረስ ይኖርበታል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

ለዚህም ክልሉ እንደመንግስት የሚጠበቅበትን ሃላፊነቱን በመወጣት ምርጫው ግልጽነትና ዴሞክራሲያነትን የተላበሰ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፦https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.