Fana: At a Speed of Life!

ህዝበ ሙስሊሙን ለመከፋፈልና አንድነቱን ለማናጋት ብሎም መንግስትና ህዝብን ለማራራቅ ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ ግለሰቦችና ቡድኖች ከድርጊቶቻቸው ሊቆጠቡ ይገባል- የሰላም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ህዝበ ሙስሊሙን ለመከፋፈልና አንድነቱን ለማናጋት ብሎም መንግስትና ህዝብን ለማራራቅ ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ ግለሰቦችና ቡድኖች ከድርጊቶቻቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር አሳሰበ።

የሰላም ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ መንግስት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች አንድነት ተጠብቆ በሰላምና በትብብር ህዝበ ሙስሊሙ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ውስጥ ሚናውን እንዲወጣ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጿል።

ለህዝበ ሙስሊሙ ሰላምና አንድነት ተገቢውን ሁሉ ዓይነት ድጋፍ አድርጓል እያደረገም ይገኛል ያለው ሚኒስቴሩ ሆኖም ግን አሁን በተለያዩ የግልና የቡድን የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች እና በተለያዩ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች የሃሰት መረጃ መሆናቸውን ህዝበ ሙስሊሙ እንዲያውቅ እንፈልጋለን ብሏል፡፡

አሁን እየተሰራጨ ያለው መረጃ እንደተቋም የሰላም ሚኒስቴር ሲያደርግ ከነበረው ያላሰለሰ ጥረት እጅግ የራቀ የሃሰት መረጃ ሲሆን ሃገራዊው ምርጫ መንግስታዊ ሰርዓት መመሰረቻና ማጠናከሪያ እንጂ ከሀይማኖታዊ አሰራር ጋር ግንኙነት የሌለው መሆኑ እየታወቀ ለራስ የግል ጥቅም በሚመች መንገድ መልዕክት እያዘጋጁ ሙስሊሙን ህብረተሰብ ለማደናገር የሚደረግ ጥረት ተገቢነትም፣ እውነትነትም፣ ተቀባይነትም እንደሌለው ለመግለጽ እንወዳለን ሲል ነው የገለፀው።

መንግስት ህዝበ ሙስሊሙ ህዝቡ በመረጠው በራሱ አመራርና አደረጃጀት መስራት እንዲችል በተለያዩ ጊዚያቶች የነበሩ ልዩነቶችን በማጥበብ አንድነታቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ ሰፊ ጥረት በማድረግ እንዲሁም ከተቋቋመው ጊዜያዊ ኮሚቴ ጋር በቅርበት በመስራት የሙስሊሙን ህብረተሰብ የአንድነት ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛውን የአጋዥነት ሚና የተጫወተ መሆኑ አስታውቋል።

በተጨማሪ ለበርካታ ዘመናት የሙስሊሙ  ህብረተሰብ ጥያቄዎች የነበሩ በተለይም የእስልምና ምክር ቤቱ እንደ ማህበር ከሚታይበት አሰራር ተላቆ ህጋዊ መሰረት ያለው ተቋም እንዲሆን በአዋጅ እንዲቋቋም፣ እስላማዊ ባንክ እንዲፈቀድ፣ የመስገጃ ቦታ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ሰፊ ስራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በየወቅቱ ከእስልምና ጉዳዮች ወደ ተቋማችን የሚመጡ የድጋፍ ጥያቄዎች ህግና ስርዓትን ተከትለው ተገቢው አዎንታዊ ምላሽ እንዲያገኙ ሲደረግ መቆየቱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

በሂደቱም በመጅሊሱ ቦርድ እና የዑለማዎች ምክር ቤት መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት በተለያዩ ጊዜያቶች ለመስሪያ ቤቱ በቀረቡለት ተደጋጋሚ የድጋፍ ጥያቄዎች መሰረት የሚመለከታቸውን አካት ሁሉ በማካተት በተደጋጋሚ በተናጠልና በቡድን በማነጋገር፤ አንድነታቸው ላይ ትኩረት በማድረግ ልዩነታቸውን በማጥበብና አስቀድመው ችግራቸውን በምክክር ፈትተው በጋራ ህዝባቸውን እንዲያገለግሉ በተለያየ ጊዜ እርቅና ስምምነት እንዲወርድ በመምከርና አቅጣጫ በማስቀመጥ ድጋፍ ሲደረግ እንደቆየም ነው የገለፀው፡፡

በዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አብዛኛውን ጊዜ በሁሉም ወገን የታዩ ጉድለቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ስምምነት  በመድረስ ረገድ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግና ሲያበረታታ የቆየ ቢሆንም የተቀመጡና በጋራ ስምምነት የተደረሰባቸው አቅጣጫዎችና የመፍትሄ ሃሳቦች በሁለቱም ወገኖች በኩል ሊተገበሩ አልቻሉም ብሏል።

ህዝበ ሙስሊሙን የመምራት ሃላፊነት የተጣለባቸው አካላትም በቅድሚያ በመካከላቸው ያለውን የተከፋፈለ ሃሳብ መልክ አስይዘው በመግባባትና የሚመለከታቸውን አካላት በማሳተፍ የጋራ ጠቅላላ ጉባዔ በአስቸኳይ ጠርተው በጋራ በመምከር ከዚህ ቀደም በስምምነት የፀደቁ ሰነዶችን ወደ ተግባር እንዲያሸጋግሩ እንዲደረግ፤ መግባባት ያልተደረሰባቸውን ጉዳዮች ግን በጋራ መድረክ በምክክር እንዲፈቱ አቅጣጫ በማስቀመጥ፣ ተቋማዊ አሰራሮች ተጠናክረዉ እንዲቀጥሉ ሙስሊሙ ማህበረሰብ አንድነቱን ጠብቆ ችግሩን በራሱ እንዲፈታ ሚኒስትቴሩ ሲያሳስብ እና ሲመክር ቆይቷል።

ይሁን እንጂ ጉዳዩ በመሠረታዊነት የመጅሊሱ ዉስጣዊ ችግር እንደሆነ ህዝበ ሙስሊሙ የሚረዳው ሲሆን ሰላም ሚኒስቴር ላለፉት ጊዜያቶች ችግሩ እንዲፈታ በተጠየቀው ድጋፍ መሠረት በርካታ ድጋፎችን ሲያደርግ እንደቆየም  ገልጿል።

ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን ማጥበብ ከማንኛውም ተግባር ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲሰራ የሰላም ሚኒስቴር ደጋግሞ ያስገነዘበው ጉዳይ መሆኑን ያመላከተው መግለጫው ነገር ግን በሁለቱም በኩል ያለው መካረር ለችግሩ መፍትሄ ከማስቀመጥ ይልቅ በሁለቱም ወገኖች መካከል ያለው መካረር ችግሩን እያሰፋው ያለ መሆኑን አሁን ያለበት ሁኔታን በግልጽ ያሳያል።

እስካሁን ባለው ሁኔታ መፍትሄ በማፈላለግ በሂደቱ ሲሳተፉ የነበሩ አካላት በጋራ ስምምነት የተደረሰባቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ በየፊናቸው ሲያፋርሱ እና ልዩነቱን ሲያሰፉት የቆዩ መሆናቸውን ህዝበ ሙስሊሙ ሊያውቀው ይገባል ብሏል መግለጫው።

በመሆኑም በተለያዩ ጊዜያት በተለይም በትናንትናዉ እለት በተለያዩ ግለሰቦች ማህበራዊ ድረ ገፆች እና በአንዳንድ ሚዲያዎች እየተላለፉ ያሉ የተሳሳቱ መረጃዎች የሰላም ሚኒስቴር የማያውቃቸው እና እያቀረቡት ባለው መልክ አስተያያትም ሆነ መልስ ያልተሰጠባቸው እንደሆኑና በአንፃሩ ሁለቱም ወገኖች ችግራቸውን በምክክር እንዲፈቱ ሲደረግ የቆየውን ከፍተኛ  ጥረት ህዝበ ሙሰሊሙ እንዲረዳ እናስታውቃለን ሲል በመግለጫው ላይ አስፍሯል።

በዚህ መልኩ ህዝበ ሙስሊሙን ለመከፋፈልና አንድነቱን ለማናጋት ብሎም መንግስትና ህዝብን ለማራራቅ ሀሰተኛ መረጃ በግል የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችና በተለያዩ ሚዲያዎች የሚያሰራጩ ግለሰቦችና ቡድኖች ከድርጊቶቻቸው እንዲቆጠቡ ሚኒስቴሩ አሳስቧል።

ህዝበ ሙስሊሙም በሃሰተኛ መረጃ እንዳይደናገርና  ትክክለኛ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ ሰላሙን እና አንድነቱን ጠብቆ እንዲሄድ ጥሪ አቅርቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.