Fana: At a Speed of Life!

ህዝቡ ለችግኝ ተከላው ያሳየውን ርብርብና ተሳትፎ በእንክብካቤውም መድገም እንደሚገባ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 17 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህዝቡ ለችግኝ ተከላው ያሳየውን ርብርብና ተሳትፎ በእንክብካቤውም መድገም እንደሚገባ ጥሪ ቀረበ።
ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ የሚገኘውን የአረንጓዴ ልማትና የችግኝ ተከላን ወይም ‘አረንጋዴ አሻራን’ የእስካሁን አፈፃፀምና የቀጣይ አመታት ዕቅድ ላይ ግምገማዊ ውይይት በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
በዚህ መድረክ ላይ ህዝቡ ለሀገራዊ ችግኝ ተከላ ያሳየውን ርብርብና ተሳትፎ በችግኞች እንክብካቤውም አጠናክሮ በመቀጠል ችግኞቹ የታለመላቸውን ዓላማ እንዲያሳኩ ማድረግ እንደሚገባ ጥሪ ቀርቧል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአካባቢ፣ የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ÷ የደን ሀብት መመናመን፣ የሥርዓተ ምዳር መናጋት እና የአየር ንብረት ለውጥ እየተባባሰ መምጣት እያስከተላቸው የሚገኙትን ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን ከግምት በማስገባት መንግስት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ አገራዊ “የአረንጓዴ አሻራ” መርሀ-ግብርን መዘርጋቱን አስታውሰዋል።
በዚህም ቀደም ብሎ የተጀመረውን ሀገራዊ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስልት አፈፃፀም በተሻለ ሁኔታ ለማሳካት የሚረዳ ተግባር እየተፈፀመ ይገኛል ብለዋል።
በሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ በጎ ጅማሮ በርካታ ሀገራዊ ፋይዳዎችን እያስገኘ መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነሩ÷ የዘርፉን መሠረታዊ ፋይዳ በመገንዘብም መንግስት ህዝቡን ከዳር እስከ ዳር ያነቃነቀውና መላውን አለም ያስደነቀውን ይህንን ተግባር በቀጣይ አመታትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩም በፌደራልና በክልል ዘርፍ መስሪያ ቤቶች ደረጃ በተዋቀሩ አበይትና ቴክኒክ ኮሚቴዎች አስተባባሪነት በተመራው በዚህ መድረክ ላይ በሁሉም ክልሎች የእስካሁን አፈፃፀምና ቀጣይ የስራው እቅዶች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
በተጨማሪም በእስካሁኑ ሂደት የተገኙ እውቀቶችና ተሞክሮዎችን በመለዋወጥና ድክመቶችን በማስወገድ የቀጣይ አመታት እቅድን ማሳካት ስለሚቻልበት ሁኔታ ተመክሯል።
በ2013 በጀት ዓመትም ካለፉት ሁለት ዓመታት ልምድ በመውሰድ የ5 ቢሊየን ችግኞች ተከላን ዕቅድ ለማሳካት ይቻል ዘንድ እስካሁን ባለው የዝግጅት ጊዜ ከመሬት ዝግጅት፣ ከችግኞች ዘር ዝግጅትና ስርጭት፣ ከችግኝ ማፍላትና ሌሎች አስፈላጊ ስራዎች ረገድ በመላ ሀገሪቱ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ከአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.