Fana: At a Speed of Life!

ህዝቡ በፀጥታ ስራ ላይ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ ለማጠናከር የሚረዳ የገለልተኛ አማካሪ ቡድን በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ተመሰረተ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 17 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህዝቡ በፀጥታ ስራ ላይ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ ለማጠናከር የሚረዳ የገለልተኛ አማካሪ ቡድን በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ መመስረቱንየአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
በምስረታው ላይ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው የገለልተኛ አማካሪ ቡድኑ ዋና ሰብሳቢ እንዲሁም አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ተመርጠዋል።
ቀሪ የኮሚቴ አባላትን ለመምረጥና መደበኛ የግንኙነት ጊዜን ለመወሰንና እቅድ ለማዘጋጀት ለታህሳስ 23 ቀን 2013 ዓ/ም ቀጠሮ መያዙም ነው የተገለጸው።
በምስረታ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት በሰላም ሚኒስቴር የህግ ማስከበር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬነሽ ሽባባው÷ ህዝቡ ለፀጥታ ስራ ስኬታማነት እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ ለማጠናከር በተለይ ደግሞ የፖሊስን አገልግሎት ለማዘመን የሚያስችል የፖሊስ ዶክትሪን መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡
ዶክትሪኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ተቀራራቢ ፖሊሳዊ አገልግሎትና አፈፃፀም እንዲኖር በማስቻል ማህበረሰቡ ከፖሊስ ጋር ተቀናጅቶ የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነትን በባለቤትነት እንዲወጣ ያግዛልም ብለዋል ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው÷ ህብረተሰቡ በፀጥታ ስራ ላይ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ በማጠናከርና የተሻለ ፖሊሳዊ ተቋም ለመገንባት ፖሊስን የሚያማክሩና የሚደግፉ የገለልተኛ አማካሪ ቡድን ከቀጠና ጀምሮ መቋቋሙን አስታውሰዋል።
የአማካሪ ቡድኑ መደራጀትም ደረጃውን የጠበቀና ብቃት ያለው የፖሊስ ተቋም ለመገንባት የራሱ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽነሩ አያይዘውም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለገለልተኛ አማካሪ ቡድኑ ስራ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀው ÷ በህዝብ ተሳትፎና በፈቃደኝነት የተመረጡ የገለልተኛ አማካሪ ቡድን አባላት የህዝብ ጆሮና ዓይን በመሆን በህዝብና በፖሊስ ተቋም ያለው ትስስር እንዲጠናከር ሊሰሩ እንደሚገባ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የገለልተኛ አማካሪ ቡድኑ ምክትል ሰብሳቢ ሆኖ የተመረጠው አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ÷ በህግ የበላይነት ላይ ህዝባችን የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ የተለያዩ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቀሶ በተጣለበት ኃላፊነትም ይህንን ለማሳካት ጥረት እንደሚያደርግ ተናግሯል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ወርክና ሶሻል ዴቨሎፕመንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ኮማንደር ደመላሽ ካሳዬ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፖሊስ ዶክትሪንን እና የማህበረሰብ ደህንነት ፓትሮል ቅኝትን አስመልክቶ የመወያያ ፅሁፍ አቅርበው ውይይት የተደረገ ሲሆን ከተወያዮች ለተነሱ ጥያቄዎች ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡
አስተያየታቸውን የሰጡን የውይይቱ ተሳታፊዎች ውይይቱ መደረጉና በተለይ ደግሞ በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ገለልተኛ አማካሪ ቡድን መመስረቱ ለፀጥታው ስራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል።
መንግስት ዓለም አቀፋዊና ተወዳዳሪ እንዲሁም በህግ የበላይነት የሚተዳደር የፖሊስ ተቋም ለመገንባት እየሰራ ያለው ስራ የሚያበረታታ መሆኑን በመጥቀስ የዜግነት ድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ ነን ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.