Fana: At a Speed of Life!

ህግ የማስከበር ኃላፊነት የስራ አስፈጻሚውና የህግ አውጪው ብቻ አይደለም-ያፓርላማ አባላት

የህግ የበላይነትን የማስከበር የስራ አስፈጻሚውና የህግ አውጪው ኃላፊነት ብቻ ባለመሆኑ ሁሉም አካል የድርሻውን እንዲወጣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አሳሰቡ።

አባላቱ በኢትዮጵያ ሰላም የማስፈንና ወንጀለኞችን በሕግ ቁጥጥር ስር ማዋል  ቅድሚያ ሊሰጠው  የሚገባ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ ቦታዎች ወንጀለኞችን አሳልፎ ላለመስጠትና ለመሸፈን የሚደረጉ ጥረቶች ለማንም የማይጠቅም ተግባር እንደሆነ  ነው የተናገሩት።

ምክር ቤቱ በሀገሪቱ የሕግ የበላይነት እንዲከበር ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ መሆኑን ያስታወሱት አባለቱ፥ በህግ አውጪውና በስራ አስፈጻሚው ብቻ የሚደረግ ጥረት ውጤት እንደማያመጣ አመልክተዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እንዳለበት ማሳሰባቸውን  ኢዜአ ዘግቧል።

አስተያየታውን ከሰጡት የምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ አለባቸው ላቀው ፥የሕግ የበላይነት መረጋገጥ አለበት፤ ይሔ መንግስትም የመንግስት አካል ስለሆነብቻ ሳይሆን ሰዎች በነፃነት ያለ ስጋት መንቀሳቀስ አለባቸው ብለዋል”

የሕግ የበላይነት ሊከበር የሚችለው ተጨባጭ መረጃና ማስረጃን በማሰባሰብ  መሆኑን  የሚናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ብርቱካን ሰብስቤ ናቸው፡፡

ትናንት በተካሄደው 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ ላይ በመገኘት ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ ማብራሪያና ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዜጎች የህግ ጥሰትን እያዩ በዝምታ ማለፍ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል።

የሕግ ጥሰት ወገን፣ ዘርና ድንበር የሌለው መሆኑን ገልጸው፤ ወንጀለኛ ከጥፋቱ እንዲማር ማድረግ እንጂ መሸፋፈን ጎጂ እንደሆነ አመልክተዋል።

በመሆኑም ማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል ወንጀለኛን ለሕግ ለማቅረብ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት ወንጀለኞችን አሳልፎ በመስጠት በኩል በየደረጃው ያሉ አካላት በሚፈለገው መልኩ ትብብር አለማድረግ የህግ የበላይነትን ለማስከበር የሚሰራውን ስራ ፈታኝ እንዳደረገው መግለጹ ይታወሳል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.