Fana: At a Speed of Life!

ለሁለት ቀናት የተካሄደው የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ኮንፈረንስ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ለሁለት ቀን ያካሄደውን የከፍተኛ አመራሮች ውይይት መጠናቀቁንና በውይይቱ የተነሱ ጉዳዮች አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር በሰጡት መግለጫ ፓርቲው በሁለት ዓመት የለውጥ ጉዞ ፣ ብልፅግና ፓርቲ ከመምጣቱ በፊትና ከመጣ በኋላ ስለመጣው ለውጥ መወያየቱን ገልፀዋል።

ለውጡ የሁሉም የሀገሪቱ ህዝቦች መሆኑን መገምገሙንና በቀጣይ ለውጡን ለማስቀጠልና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከሌሎች ክልሎች ጋር በጋራ እንደሚሰራ ነው የተናገሩት።

በክልሉ ህገወጥ አደረጃጀት በማፍረስ እና ህገ ወጦችን ለህግ በማቅረብ በኩል የተሰራው ስራ በመድረኩ በጥሩ መልኩ መነሳቱን ገልፀዋል።

ክልሉ አሁን ላይ ሰላሙ የተረጋገጠ መሆኑንና በቀጣይ የቱሪዝም ልማት ለማከናወን በውይይቱ መነሳቱን አብራርተዋል።

ሌላው የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በኦነግ ሸኔና ህወሃት ሴራ በዜጎች ላይ የተፈፀመውን ግድያና የሀብት ውድመት ፓርቲው ማውገዙን አቶ አገኘሁ ገልፀዋል።

የኦሮሚያ ክልል መንግስትን ህግ የማስከበር ስራ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት እንደሚያደንቅና እውቅና እንደሚሰጠው አቶ አገኘሁ ተናግረዋል።

በፓርቲው አመራር በቅርቡ ተናግሯል ተብሎ በወጣው መረጃ ዙሪያ መረጃ ለምን አሁን ወጣ? የሚለው በጥንቃቄ ለመገምገም ተሞክሯል ብለዋል።

ይሁንና በአመራሩ የተነሱት ሀሳቦች በይዘትም ስህተት መሆኑንና በፓርቲ ደረጃ በዝርዝር መገምገም እንዳለበት አይተናል ብለዋል።

የአማራና የኦሮሞን ህዝቦች መልካም ግንኙነት ማንም አይበጥሰውም ያሉት አቶ አገኘሁ በየትኛውም መንገድ የማይወዛወዝ ወንድማማችነት ያላቸው ህዝቦች ናቸው ብለዋል።

በተመሣሣይ ከትግራይ ወንድማማች ህዝቦች የአማራን ህዝብ ህወሃት ሊነጥለው እንደማይችልም ነው የተናገሩት።

ከዚህ ባለፈ በአማራ ብልፅግና ፓርቲ አመራሮች መካከል ልዩነት ተፈጥሯል የሚለው መሰረተ ቢስ መሆን በመግለፅ የአመራሩን አንድነት ለመለያየት በማህበራዊ ሚዲያዎች የተከናወነ ነው ብለዋል።

አመራሩ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አንድ መሆኑንም አንስተዋል።

በናትናኤል ጥጋቡ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.