Fana: At a Speed of Life!

ለህወሓት ጸረ ሰላም ቡድን በድብቅ ምሽግ ሲሰሩ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል የተባሉ የመከላከያ መኮንኖች ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ለህወሓት ጸረ ሰላም ቡድን የኮንስትራክሽን ስራ በሚል በድብቅ ምሽግ ሲሰሩ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል የተባሉት ሌተናል ኮሎኔል ኤፍሬም አብርሃን ጨምሮ 7 የመከላከያ መኮንኖች ፍርድ ቤት ቀረቡ።
ተጠርጠሪዎቹ የመከላከያ ዶዘር ኦፕሬተር ሌተናል ኮሎኔል ኤፍሬም አብርሃ፣ 2ኛ ኮሎኔል ገብረ ጊዮርጊስ ገብረሚካኤል፣ ኮሎኔል ፍስሃ ግደይን ጨምሮ በአጠቃላይ 7 ተጠርጣሪዎች ናቸው ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው የታየው።
በተጠረጠሩበት ሃገርን በመካድ ህገመንግስቱን እና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ለመናድ ሙከራ ወንጀል መርማሪ ፖሊስ ያከናወነውን የምርመራ ስራ ለችሎቱ አብራርቷል።
ተጨማሪ ሶስት የምስክር ቃል ተቀብሎ ከምርመራ መዝገቡ ጋር ማያያዙንም ገልጿል።
በተለይም በአንደኛ ተጠርጣሪ ላይ በተደረገ ምርመራ በተለያዩ ቦታዎች የትግራይ ልዩ ሃይል የመከላከያ ሰራዊትን ማጥቃት የሚቻልበትን ቦታ በመለየት ምሽግ ሲቆፍርና ሲያስቆፍር እጅ ከፍንጅ ተይዟል ያለው መርማሪ ፖሊስ ይሄው ተጠርጣሪ የወንጀሉ ተሳትፎ እንዳለው በሰው ምስክር ማረጋገጡንም አብራርቷል።
ከ2ኛ አስከ 7ኛ ተራ ቁጥር በመዝገቡ የተካተቱ ተጠርጣሪዎችም ጥቃቱ ከመሰንዘሩ በፊት የሰሜን እዝ መከላከያ ሬዲዮን የማቋረጥ በየደረጃው ተሳትፎ የነበራቸው መሆኑን በመረጃ አረጋገጫለሁ ብሏል ።
ከተጠርጣሪዎቹ የተከሳሸነት ቃል መቀበሉን የገለጸው መርማሪ ፖሊስ ለቀሪ የምርመራ ተጨማሪ 14 ቀን ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎቹ ሃገርን በታማኝነት ያገለገሉ መሆናቸውን ለችሎቱ ገልጸው በወንጀሉ ተሳትፎ እንደሌላቸው የተከራከሩ ሲሆን በዋስ እንዲፈቱም ጠይቀዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱ መርማሪ ፖሊስ ከጀመረው ምርመራ አንጻር ተጨማሪ ቀናት እንደሚያስፈልገው ከግምት ውስጥ በማስገባት 11 ተጨማሪ ቀናትን ለምርመራ ፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.