Fana: At a Speed of Life!

ለህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ደመናን የማበልፀግ ቴክኖሎጂ የመጠቀም ዕቅድ ተይዟል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ከመደበኛ ዝናብ በተጨማሪ ደመናን የማበልፀግ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ዕቅድ መያዙን ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።

የግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተያዘው ዓመት የክረምት ወራት ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።

የግድቡን የውሃ ሙሌት ለማሳካት ከመደበኛ ዝናብ በተጨማሪ ደመናን በማበልፀግ የማዝነብ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ዕቅድ መያዙን ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታውቋል።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ክንፈ ሃይለማርያም እንደገለጹት፥ በቅርቡ በተጀመረው ደመናን የማበልፀግ ቴክኖሎጂ በአገሪቱ ያሉ አሥር የተለያዩ ተቋማት ተሳትፈዋል።

ደመናን ለማበልፀግ በመጀመሪያ በከባቢ አየር ውስጥ ለመበልፀግ በቂ የሆነ ደመና መኖሩን ማረጋገጥ እንደሚገባ የገለጹት አቶ ክንፈ፣ ቴክኖሎጂውን ለተለያዩ ሀገራዊ ጥቅሞች ማዋል ይቻላል ብለዋል።

በመሆኑም ኤጀንሲው ደመናን ለማበልፀግ አመቺ የሆነውን ጊዜ ከመተንበይ ባለፈ ከበለፀገ በኋላ የተገኘውን የዝናብ መጠን ጭማሪ ይገመግማል ብለዋል።

ደመናን በማበልፀግ ቴክኖሎጂ የሚገኘው ተጨማሪ ዝናብ በሰብል ልማት ሊያጋጥም የሚችለውን የዝናብ እጥረት ችግር የሚያቃልል መሆኑንም ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው ከሰብል ልማት በተጨማሪ ግድቦችን ለመሙላት፣ የመብረቅ አደጋን ለመቀነስና ለሌሎች ጠቀሜታዎች ይውላል ነው ያሉት።

ደመናን በማበልፀግ የሚገኘውን ዝናብ በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ ዝርዝር ጥናት ወደ ፊት ይካሄዳልም ብለዋል።

የክረምቱ የአየር ትንበያ በአባይ ተፋሰስና በምዕራብ ኢትዮጵያ አጋማሽ ከመደበኛና መደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖር ግምት መኖሩንም አቶ ክንፈ ጠቅሰዋል።

ይህ እንዳለ ሆኖ የሕዳሴ ግድብን ለመሙላት ከመደበኛ ዝናብ በተጨማሪ ውሃ የሚያስፈልግ ከሆነ ደመና የማበልፀግ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም እቅድ ተይዟል ብለዋል።

በዓለም አቀፉ የአየር ጠባይና ኅብረተሰብ ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ዶክተር ቱፋ ድንቁ፥ ቴክኖሎጂው ደመናን ወደ ዝናብ ለመቀየር ከማስቻሉ በተጨማሪ ዝናብ በሚፈለግበት ቦታ እንዲዘንብ ያስችላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.