Fana: At a Speed of Life!

ለልማት አጋሮች በትግራይ ክልል ስለተካሄደው የህግ ማስከበርና መልሶ የማቋቋም እንቅስቃሴ ማብራሪያ ተሰጠ

አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 12 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ እና የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በኢትዮጵያ ለሚገኙ የልማት አጋሮች ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በትግራይ ክልል ስለተካሄደው የህግ ማስከበርና መልሶ የማቋቋም እንቅስቃሴ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በዚህ ወቅት አቶ አህመድ ህግ የማስከበር እርምጃው የሰላማዊ ሰዎችን ህይወት ለአደጋ በማያጋልጥ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸው የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ እርዳታ ጥረቱን በመደገፍ ረገድ የልማት አጋሮች ያበረከቱትን አስተዋፅኦ አድንቀዋል፡፡
ሁሉም የልማት አጋሮች ኢትዮጵያ የቀጠናው የሰላም ማእከል እንድትሆን ከጎኗ እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አቶ አህመድ አያይዘውም በትግራይ ክልል ሀላፊነት በማይሰማው ወንጀለኛው ቡድን የወደሙትን የትራንስፖርት፣ የውሀ፣ የኤሌክትሪክና የቴሌኮሙኒኬሽን መሰረተ-ልማቶችን በመጠገን ክልሉን መልሶ በማቋቋም ወደ ነበረበት የመመለስ ጉዞ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡
የመሰረተ ልማቶቹ መውደም ምግብና መድሀኒት የመሳሰሉትን የሰብአዊ ድጋፎችን ለማድረስ ጊዚያዊ ድልድዮችን በአስቸኳይ መገንባት የጠየቀ በመሆኑ በሰብአዊ ድጋፉ ምላሽ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩንም አመልክተዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደርም የከተማ አስተዳደሮችን በማዋቀር ከቀበሌ ጀምሮ እስከላይ መዋቅር በመዘርጋት የተሻለ የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽነትና አፈጻጸም እንዲኖር ቁልፍ ሚና መጫወቱንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ከተባበሩት መንግስታት ጋር በቅንጅት የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ለትግራይ ክልልና ጉዳት በደረሰባቸው አጎራባች የአማራና የአፋር ክልሎች ሲያከናውን መቆየቱን አሰረድተዋል፡፡
በአንዳንድ ወረዳዎች የባንክ አገልግሎት በመጀመሩ፣ በአካባቢ ላሉ ገበያዎች አስፈላጊ ሸቀጦች ተደራሽ እንዲሆኑ ጥረት በመደረጉና የብሄራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለ1 ነጥብ 8 ሚሊየን የክልሉ ህብረተሰብ የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ማድረግ በመቻሉ በክልሉ ህይወት ወደቀድሞው ሁኔታ እየተመለሰ መሆኑ መገለፁን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.