Fana: At a Speed of Life!

ለምርጫው ስኬታማነት ጋዜጠኞች ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ለስድስተኛው ሃገራዊና ክልላዊ ምርጫ ስኬታማነት ጋዜጠኞች ሙያዊ ስነ ምግባርን በማክበር ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።

ምክር ቤቱ በባህር ዳርና አካባቢዋ ለሚገኙ ጋዜጠኞች የምርጫ የስነ-ምግባር መመሪያዎችን በተመለከተ ስልጠና ሰጥቷል።

የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሞላልኝ መለሰ ለኢዜአ እንደገለጹት መገናኛ ብዙሃን ለምርጫ ፍትሃዊነትና ዴሞክራሲያዊነት የጎላ ሚና አላቸው።

በኢትዮጵያ ቀጣይ የሚካሄደው ሃገራዊና ክልላዊ ምርጫ ለሃገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት በመጥቀስ፤“የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ሙያዊ ስነ ምግባራቸውን አክብረው ሊሰሩ የግድ ይላል”ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀውን መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች ምርጫውን ለመዘገብ የሚያስችል መመሪያ ጋዜጠኞች መመሪያውንና ኤዲቶሪያል ፖሊሲያቸውን መሰረተ ባደረገ መልኩ ያለ አድልኦ ሊዘግቡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

“ጋዜጠኛ ብሄር የለውም” ያሉት አቶ ሞላልኝ፤ ለየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ሳይወግን ወገንተኝነቱን ከእውነት ጋር ብቻ ሊያደርግ እንደሚገባም ገልጸዋል።

በምርጫ ወቅት የሃገርን ሰላም ሊረብሽ በሚችል መልኩ እንዳይሆን ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው የገለጹት ደግሞ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድን የሚያግዝ ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን ፎር ኢሌክቶሪያል ሲስተም ተቋም የህግ ባለሙያ አቶ ሰለሞን ግርማ ናቸው።

ብሄርን ከብሔር፣ ፓርቲን ከፓርቲ ሊያቃቅሩ ከሚችሉ ዘገባዎች በመቆጠብ ለምርጫው ሰላማዊነትና ዴሞክራሲያዊነት ሙያዊ ሃላፊነትን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባም አመልክተዋል።

ሙያዊ ስነ-ምግባሩን ሳያከብር በሚሰራ ጋዜጠኛና መገናኛ ብዙሃን ላይ ምርጫ ቦርድ የሚወስደው እርምጃ እንዳለ ሆኖ ምክር ቤቱ በግልግል ዳኝነት በሚቀርቡ ጉዳዮች ዙሪያ ውሳኔ ይሰጣልም ነው ያሉት።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.