Fana: At a Speed of Life!

ለምግብ እህል እጥረት መፍትሄ ይዞ የመጣው የከተማ ግብርና

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዓለም ዙሪያ ሰዎች የኢኮኖሚ እድሎችን ለመፈለግ ከቦታ ቦታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መጨመሩን ተከትሎ በዓለም ዙሪያ ከተሞች በፍጥነት እያደጉ መጥተዋል።

ይህ የሰዎች እንቅስቃሴ በቀጣይ ጊዜያትም እየጨመረ እንደሚመጣ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው በፈረንጆቹ 2018 ላይ 55 በመቶ የዓለማችን ነዋሪ ከተሜ ሆኗል። ይህ አሃዝ በምዕተ ዓመቱ እኩሌታ ላይ 68 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

ከተሞች የሀገራት የፋይናንስ፣ የባህል እና የፖለቲካ ማዕከል መሆናቸው እሙን ነው። እነዚህ ከተሞች የዓለምን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ እና የመመገብ ሚና ይኖራቸዋል ወይ? ለሚለው ጥያቄ ኔቸር ፉድ የተባለ ጋዜጣ በቅርቡ ይፋ የሆነን ጥናት መሰረት አድርጎ ምላሹ አዎ የሚል ነው ይላል።

በሼፊልድ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው በከተሞች የሚገኙ 10 በመቶ የአረንጓዴ ስፍራዎችን ተጠቅሞ የከተማ ግብርና በማከናወን 15 በመቶ የምግብ ፍላጎትን መሸፈን እንደሚቻል ያመለክታል።

የዩኒቨርሲቲው የዘላቂ ምግብ ኢንስቲትዩት ተወካይ የሆኑት ጂል ኤድመንሰን ለሲ ኤን ቢ ሲ እንደተናገሩት፥ በተለይም አትክልት እና ፍራፍሬዎች ልማት ለከተማ ግብርና እጅግ አመቺዎች ናቸው።

ባለሙያዋ በከተማ የሚከናወኑ የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማቶች ለነዋሪዎች ትኩስ ምርት እንዲቀርብ በማድረግ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጡ ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

እንደባለሙያዋ ማብራሪያ በከተሞች በግለሰቦች ደረጃ ባሉ የአትክልት ስፍራዎች ላይ ሰዎች የሚወድቱን የአትክልት ወይም ፍራፍሬ ዓይነት በመምረጥ ባለቻቸው ውስንና ጠባብ ቦታዎች በቀላሉ ሊያለሙ ይችላሉ።

ሆኖም የእህል ምርቶችን በከተሞች አካባቢ ለማልማት ሰፊ የእርሻ ቦታን እና ለማቀነባበር የሚሆን አካባቢን የሚፈልግ መሆኑን አንስተዋል።

እንደተመድ መረጃ 821 ሚሊየን ሰዎች በዓለም ዙሪዩ በቂ እና የተመጣጠነ መግብ አያገኙም። በመሆኑም በከተሞች አካባቢ በሚከናወን የግብርና ስራ ግን እንደነዚህ ዓይነቶችን ዜጎች ለመቅረብም ከተሞችም በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ እንደሚቻል ያስረዳሉ።

ሆኖም ግን የከተማ ግብርናን ለማከናወን እንቅፋት የሚሆኑ የኢኮኖሚ፣ የምህንድስና እና የባህል ተግዳሮቶችን ለመፍታት በአካባቢ እና በብሄራዊ ደረጃ የሚገኙ ፖሊሲ አውጪዎች ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ይላሉ።

የሲ ኤን ቢ ሲ ዘገባ ሀይድሮፎኒክስ የተባለው አዲስ ቴክኖሎጂ ምንም ዓይነት አፈር እና የተፈጥሮ የጸሃይ ብርሃንን መጠቀም ሳያስፈልግ በቤት ውስጥ አትክትልና ፍራፍሬን ማልማት የሚያስችል አዲስ እድል ይዞ ማምጣቱንም አንስቷል።

በዚህ ቴክኖሎጂ በኩል ሰዎች አሁን ላይ የቤታቸውን ጣሪያ ወይም የመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የሚገኝ አነስተኛ ስፍራን በመጠቀም ቲማቲምን ጨምሮ ሌሎች የጓሮ አትክልቶችን እያለሙ ትኩስ፣ በማእድን የበለፀገ ጤናማ አትክልትን ከጓራቸው እየቀነጠሱ መጠቀምን ጀምረዋል ብሏል።

በአዲስ አበባ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከተማዋ አስተዳደር የከተማ ግብርናን ለማበረታታት ሰፊ ዘመቻ መክፈቱ ይታወቃል።

ነዋሪዎች በጓራቸው ባላቸው ክፍት ስፍራ የቻሉትን ያሀል አትክልትና ፍራፍሬ የማልማት እና ዶሮ የማርባት ስራ እንዲያከናውኑ ከማበረታታት ባለፈ በከተማዋ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች መዲናይቱን እንዲመግቡ በሚያስችል የከተማ ግብርና ስራ እንዲሰማሩ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.