Fana: At a Speed of Life!

ለሰላም መጠናከርና ህገወጥ ተግባራትን ለመታገል ከመንግስት ጎን ሆነው እንደሚሰሩ የሶማሌ የአገር ሽማግሌዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሰላም፣ ፀጥታ መጠናከርና ህገወጥ ተግባራትን ለመታገል ከመንግስት ጎን ሆነው እንደሚሰሩ የሶማሌ ክልል የአገር ሽማግሌዎች ተናገሩ፡፡

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ በዛሬው ዕለት ከክልሉ የአገር ሽማግሌዎች ጋር ተወያይተዋል ።

በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ እና በሶማሌ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር መሐመድ ሻሌ የተመራ የአገር ሽማግሌዎች በጋራ የተደረገው ምክክር መድረክ በከተማና በድንበር አካባቢ ያለው ሰላምና ፀጥታ ሁኔታ፣ እየናረ የመጣው የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር የሚቻልበት መንገድ ፣ የነዳጅ እጥረትና ተያያዥ ችግሮች እና የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥን የበለጠ ማጠናከርን አላማው ያደረገ ነው ተብሏል።

ተሳታፊ የአገር ሽማግሌዎችም መንግስት በሰላምና ፀጥታ ማስፈን ላይ ከከተሞች አንስቶ እስከ ድንበር ድረስ እየሰራ ያለው ትልቅ ስራ የሚበረታታና ሁሉም የፀጥታ አካል በያለበት መስክ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ።

በተለይም ከከተሞች ዕድገት እና መስፋት ጋር ተያይዞ መንግስት በከተሞች አካባቢ ያለውን የፀጥታ ተቋማትን የበለጠ ማስፋትና ማጠናከር እንደሚገባ የአገር ሽማግሌዎች ተናግረዋል ።

በሌላ በኩል ከዕለት እለት እየናረ የመጣው የዋጋ ግሽበትን በተመለከተ ከቀረጥ ነፃ የተፈቀዱ የምግብ ሬሽኖችን በስፋት እንዲገቡ መፍቀድና አሁን ካለው የገበያ ስርዓት በተጨማሪ ተወዳዳሪ የሚሆኑ ምርቶችን በስፋትና በመጠን የሚያቀርቡ አስመጪዎችን ማብዛት እንደሚገባና ሰው ሰራሽ የገበያ እጥረትና ገበያው እንዳይረጋጋ የሚያደርጉ አካላትን ተከታትሎ ለህግ ማቅረብና እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ነው የተገለጸው ።

እንደመፍትሄ የክልሉ መንግስት አሁን ላይ ዕቅድ ይዞ የጀመረው የራስን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በሁሉም የክልሉ ዞኖች የግብርና እርሻ ስራ ዋና መፍትሔ በመሆኑ ክልሉ ባሉት ወንዞች ላይም ሆነ በተገኘው ዝናብ ተጠቅሞ ህዝቡ ግብርናው ላይ ጠንክሮ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

አያይዘውም በክልሉ እየተስተዋለ የመጣውን የነዳጅ እጥረት መንግስት ችግሩን ለይቶ በማጥናት አፋጣኝ መፍትሔ ሊፈልግለት እንደሚገባም አመላክተዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ በበኩላቸው ፥ ለተሰጡት የተለያዩ ሃሳብና አስተያየቶችን ጠቃሚና ጊዜውን የጠበቁ መሆናቸውን አንስተው መንግስት በተነሱት ሐሳቦች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የአገር ሽማግሌዎችም በሰላምና ፀጥታውም ሆነ ህገወጥ አሰራርን በማስረፅ በዜጎች ላይ አግባብ ያልሆነ አሰራርንና ፍትሐዊ ያልሆነ ተግባርን ከመንግስት ጎን በመሆን ሊታገሉ እንደሚገባ መግለጻቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.