Fana: At a Speed of Life!

ለህልውና ዘማቾች፥ ለዘማች ቤተሰቦችና ለተፈናቃዮች የሚደረግ ድጋፍ ቀጥሏል

 

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በመተባበር ለተፈናቃዮች እና ለወገን ጦር የሚውል ከ35 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የአልባሳት እና የምግብ ግብአት ድጋፍ አደረጉ።

ድጋፉን ያስረከቡት የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ፥ ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያ ቀያቸው ሲመለሱ የማቋቋም ስራን በስፋት እንደሚሰራ ገልፀው፤ የወገን ጦር ድል እስኪያደርግ ድጋፋችን አይለይም ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሀላፊ ዶክተር ምስራቅ መኮንን በበኩላቸው፥ ምክር ቤቱ ለተፈናቃዮቹ እና ለወገን ጦር የሚያደርገውን ድጋፍ በስፋት እንደሚቀጥልበት ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ጤና ሚኒስቴር፣ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች እንዲሁም የጎንደር ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ለሰሜን ሸዋ ዞን፣ ለህልውና ዘማቾች እንዲሁም ለዘማች ቤተሰቦች ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ጤና ሚኒስቴር ለሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር 6 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የመድሃኒት፣ የህክምና ቁሳቁስ እንዲሁም የአልባሳት ድጋፍ አድርገዋል።

ሚኒስቴሩ ድጋፉን ያደረገው ከኢትዮጵያ ሚድዋይፈሮች ማህበርና ከኢትዮጵያ የፅንስና ማህፀን ሃኪሞች ማህበር ጋር በመተባበር ሲሆን÷ ከተደረገው ድጋፍ 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የሚያወጣው የመድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህጻናት ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ÷ ከግሬስ ለህጻናት እና ወላጆቻቸው ማዕከል ጋር በመተባበር 600 ሺህ ብር ግምት ያላቸው የምግብና ምግብ ነክ ድጋፍ ለዘማች ቤተሰብ አባላት ተደርጓል፡፡

በተመሳሳይ በባህርዳር ከተማ አስተዳደር በ6 ክፍለ ከተሞችና በ14 ገጠር ቀበሌወች የስንቅ ዝግጅት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

የአሸባሪው ህወሓት ቡድን እስከሚደመሰስ ድረስ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ልዩ ሀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ የሚደረገው የስንቅ ዝግጅትና አቅርቦትን አናቋርጥም ÷ ደጀንነታችን የማይነጥፍ ምንጭ ነው ብለዋል።

የጎንደር ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ፅህፈት ቤት እንዲሁ በግንባር ለሚገኘው ሰራዊት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

የፅህፈት ቤቱ ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ወርቅነህ አያል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት÷ በግንባር ሆኖ የህይወት መስዋእትነት እየከፈለ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ እንዲሆን ነው ድጋፉን ያደረግነው ብለዋል፡፡

ድጋፉን የተቀበሉት የሰሜን ሸዋ አስተዳዳር አመራሮች፥ ተቋማቱ ላያደረጉት ድጋፍ አመስግነው መሠል ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለተፈናቃዮች የሚሆን 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ወጭ የተደረገበት ፍራሽ፣ ሩዝ፣ ዱቄት እና ማካሮኒ በባሕርዳር ተገኝቶ አስረክቧል፡፡
በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዮም መኮነን÷ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ላደረገው ድጋፍም አመስግነው÷ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ከአሚኮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

አካባቢዎን ይጠብቁ!

ወደ ግንባር ይዝመቱ!

መከላከያን ይደግፉ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.