Fana: At a Speed of Life!

ለሰባተኛው የብሄራዊ ባንክ ገዢ አቶ ዱባለ ጃሌ ህክምና የሚውል ገንዘብ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሰባተኛው የብሔራዊ ባንክ ገዢ ለነበሩት አቶ ዱባለ ጃሌ ላጋጠማቸው የጤና እክል ማሳከሚያ የሚውል የእርዳታ ገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡
 
አቶ ዱባለ ጃሌ በስልጣን ዘመናቸው በተለየ መልኩ እጃቸው ከሙስና፣ ከስርቆትና ከገንዘብ ማጭበርበር አፀያፊ ተግባራት የፀዳ እንደነበር የተመሰከረላቸው ትጉህ ሰው እንደነበሩ ተገልጿል፡፡
 
የኢትዮጵያ ባንኮች ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ የላቀ ሚናም የነበራቸው ሰው ናቸው ተብሏል።
 
አቶ ዱባለ ጃሌ በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንቶች የኢኮኖሚ አማካሪ በመሆን አገልግለዋል።
 
በአሁኑ ሰዓት ግን ባጋጠማቸው ከባድ የጤና እክል እራሳቸው ማሳከም ባለመቻላቸው ይህ የእርዳታ ገንዘብ የማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተዘጋጅቶላቸዋል።
 
ትናንት ምሽት በተካሄደው በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ጥሪ የተደረገላቸው የፋይናንስ ተቋማት አመራሮች፣ ባለሀብቶችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተገኝተዋል።
 
በዚህም አቢሲኒያ ባንክ 1 ሚሊየን ብር፣ ልማት ባንክ 500 ሺህ ብር፣ ወጋገን ባንክ 100 ሺህ ብር እና ሌሎች ባለሀብቶችም የተለያየ መጠን ያለው የገንዘብ እርዳታ ማድረጋቸው ተጠቁሟል።
 
መንግስትን ጨምሮ ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እኝህ የሀገር ባለ ውለታ ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ እገዛ ማድረግ አለባቸው ሲሉም የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.