Fana: At a Speed of Life!

ለስምንት ወራት ተስተጓጉሎ የነበረው የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ዝርጋታ ስራ ተጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 19፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ ተስተጓጉሎ የነበረው የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት ችግሩ ተፈትቶ ስራው የቀጠለ መሆኑን የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አብዱልከሪም መሃመድ ገለጹ።

የፕሮጀክቱ አካል የሆነውና በኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ችግር በመጀመርያ ምዕራፍ ግንባታው ተጠናቆ ያለአገልግሎት የቆየውን የአዋሽ – ኮምቦልቻ የባቡር መስመር በቅረቡ ስራ ለማስጀመር እየተሰራ እንደሆነም ተነግሯል ።

ስራ አስኪያጁ በሁለት ምዕራፍ እየተሰራ የሚገኘው የአዋሽ- ኮምቦልቻ- ሃራ ገበያ 390 ኪሎ ሜትር የምድር ባቡር መስመር ዝርጋታ በ2007 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በ2012 ዓ.ም መጨረሻ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እንደነበር ለኢዜአ ገልፀዋል።

የሁለተኛው ምዕራፍ ከኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ ያለው 122 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ዝርጋታም ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ አለመግባባት ስራው ተስተጓጉሎ መቆየቱን አመልክተዋል።

“በአጠቃላይ ከኤሌክትሪክ አቅርቦትና ከከሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ በሁለቱም ምዕራፎች የባቡር መስመር ዝርጋታ ስራው ለስምንት ወር ተስተጓጉሎ ቆይቷል” ብለዋል።

ችግሩን ለመፍታት በመንግስት በተቀመጠ አቅጣጫ መሰረት ለ480 አርሶ አደሮች 100 ሚሊየን ብር ተጨማሪ የካሳ ክፍያ በቅርቡ በመከፈሉ በሁለተኛው ምዕራፍ ተስተጓጉሎ የነበረው የ50 ኪሎ ሜትር መስመር ዝርጋታ ካለፈው ወር ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

ከኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ ያለው 122 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ዝርጋታ አጠቃላይ ስራ 82 በመቶ መጠናቀቁን የጠቆሙት የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ፤ ቀሪውን ስራ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በመጀመሪያ ምእራፍ ግንባታው 99 በመቶ ተጠናቆ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ወደ ሙከራ ሳይገባ የቆየውን አዋሽ – ኮምቦልቻ የባቡር መስመርን ስራ ለማስጀመር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

የባቡር መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክቱ በጊዜ መራዘም ምክንያት ተጨማሪ ወጪ እንዳይጠይቅ ባለድርሻ አካላትን በማሳታፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ የምድር ባቡር መስመር ስርጋታ ፕሮጀክት የ51 ድልድዮችና የ12 ዋሻዎች ግንባታ ያካተተ መሆኑን ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

አዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ የምድር ባቡር ፕሮጀክት በ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚከናወን መሆኑ ታውቋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.