Fana: At a Speed of Life!

ለስፖርት ውርርድ ጨዋታ አዲስ ፈቃድ መስጠት ማቆሙን የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀገሪቱ እየተስፋፋ ለመጣው የስፖርት ውርርድ ጨዋታ አዲስ ፈቃድ መስጠት ማቆሙን የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር አስታወቀ።

አስተዳደሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስታወቀው፥ ጨዋታው ላይ የተግባር ቁጥጥርን አጥብቆ ለመስራት የሚያስችለውን የአሰራር ስርዓት እስከሚዘረጋ ድረስ አዲስ ፈቃድ መስጠት አቁሟል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሰሞኑን በተከታታይ በሰራቸው ዘገባዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ይህ የስፖርታዊ ውርርድ ጨዋታ በፍጥነት እየተስፋፋ መምጣቱን ተመልክቷል።

በዚሁ የውርርድ ጨዋታ ውስጥ የሚሳተፉ ወጣቶችም ሆነ የታዳጊዎች ቁጥር ቀላል አለመሆኑንም ነው የታዘበው።

የውርርድ ተቋማት ተብለው ህጋዊ ፈቃድና እውቅና የተሰጣቸው ድርጅቶች፣ የዳበሩ ድረገፆች ያሏቸው፣ አማራጭ የአንድሮይድ መተግበሪያን የሚጠቀሙ እና አለፍ ሲልም ይህ ላልገባቸው በአዲስ አበባ እና በክልሎች የተለያዩ ቦታዎች የመወራረጃ ትኬትን መሸጣቸው ወጣቶች እና ታዳጊዎችን በቀላሉ እንዲይዙ እንዳስቻላቸው ይነገራል።

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ዙሪያም እየተስፋፋ የመጣው ይህ የውርርድ ጨዋታ በተማሪዎች ላይ አሉታዊ ተፅእኖን ወደ ማሳደሩ ተሸጋግሯል።

የመወራረጃ አማራጮቹ አነስተኛ ከተባለው 10 ብር እስከ ተወራራጁ አቅም ድረስ የሚፈቅድ መሆኑም በርካቶች በጨዋታው ሱስ በማስያዝ ለማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ቀውስ እየዳረጋቸው መሆኑን ከአስተያየት ሰጭ ወጣቶች ተረድተናል።

በኢትዮጵያ ያለው አሁናዊ መልክ አሳሳቢ መሆኑን ከወራት በፊት ያስነበበው ዓለም አቀፉ ተነባቢ መፅሄት ዘ ኢኮኖሚስት፥ “ኢትዮጵያ በቁማር በሽታ ተይዛለች” የሚል ርዕስን ሰጥቶ ለንባብ ባበቃው ዘገባ ከትንሹ 10 ብር እስከ መጠኑ ከፍ ባለ ገንዘብ የሚመደብበት የውርርድ ጨዋታው በማህበረሰቡ ዘንድ ስር የሰደደ ችግርን ይዞ ስለመምጣቱ አንስቷል።

በሀገሪቱ 22 የሚሆኑ ድርጅቶች በስፖርታዊ ውርርድ ጨዋታ ላይ ፈቃድ አውጥተው እየሰሩ ይገኛሉ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.