Fana: At a Speed of Life!

ለትግራይ ክልል መልሶ ግንባታ ከ150 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር፣ የሐረሪ ክልል እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳዳር ለትግራይ ክልል መልሶ ግንባታ ሥራ ከ150 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ።

ድጋፉን በአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦድሪን በድሪ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ቡህ የተመራ ልዑክ መቐለ ከተማ ተገኝቶ አስረከቧል፡፡

ልዑካኑ መቐለ አሉላ አባነጋ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች፣ በሃይማኖት አባቶችና በሃገር ሽማግሌዎች አቀባበል ተደርጎለታል።

የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮችና የሐረሪ ክልል ለክልሉ ያደረጉት ድጋፍ የአብሮነት መገለጫና የኢትዮጵዊነት ተምሳሌት ነው ተብሏል፡፡

በድጋፍ ርክክቡ ወቅት ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ “ራስ ወዳድ የሆነው የጥፋት ቡድን ባመጣው ችግር በህዝብ ላይ የተለያየ ጉዳት ደርሷል” ብለዋል።

“የዛሬዋ ኢትዮጵያ በዚህ መልክ እንድትቆም የትግራይ ህዝብ ዋጋ ከፍሏል” ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፤ ህግ የማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ የደረሰውን ጉዳት በኢትዮጵያውያን ትብብር መጠገን እንደሚቻል አመላክተዋል፡፡

“የከተማ አስተዳዳሩ የትግራይን ህዝብ ጉዳት ሊካፈልና ከጎኑ ለመቆም የፍቅር ስጦታ ይዞ ወደ ትግራይ መጥቷል” በማለትም ነው የገለጹት።

በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንደተገለጸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 100 ሚሊየን ብር፣ 574 ኮምፒውተሮች፣ 123 ፕሪንተሮችና የፎቶ ኮፒ ማሽኖችን ድጋፍ አድርጓል።

ከዚህ በተጨማሪ አስተዳደሩ ሦስት አምቡላንስ እና ሦስት ተሽከርካሪዎችን ድጋፍ ማድረጉንም ነው ምክትል ከንቲባዋ የገለጹት፡፡

አጠቃላይ በገንዘብና በቁሳቁስ የተደረገው ድጋፍ ከ135 ሚሊየን ብር በላይ መሆኑን ጠቁመው፤ ድጋፉ ቀጣይነት አለው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦድሪን በድሪ በበኩላቸው የክልሉ መንግስትና ህዝብ የአብሮነት፣ የወንድማማችነት እና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆነውን ድጋፍ ይዘው ወደ መቐለ ማቅናታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ክልሉ 10 ሚሊየን ብር ፣ አምቡላንስና የተለያየ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ መሐመድ ቡህ በበኩላቸው አምስት ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ድጋፉን በተቀበሉበት ወቅት እንዳሉት ክልሉን መልሶ ለመገንባት ሁሉም ሊረባረብ ይገባል፡፡

ጊዜያዊ አስተዳደሩ የትግራይ ክልልን መልሶ ለመገንባት ሥራ መጀመሩን ገልጸው፤ ለዚህም ሁሉም እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.