Fana: At a Speed of Life!

ለነዳጅ ግብይት ሪፎርሙ ውጤታማነት በትኩረት ይሰራል- ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለነዳጅ ግብይት ሪፎርሙ ውጤታማነት በትኩረት እንደሚሠራ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ፡፡
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከነዳጅ ግብይት ሪፎርም ትግበራ ጋር ተያይዞ ከሐረሪ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል።
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት÷ የክልሉ መንግሥት ሪፎርሙ ተግባራዊ እንዲሆን በቁርጠኝነት ይሰራል።
በተለይም የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማስፋትና ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር የማድረግ ስራ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
አመራሩም ከስራ ቀናት ውጪ ተሽከርካሪ ባለመጠቀም ነዳጅ በመቆጠብ አርአያ መሆንና ሪፎርሙን ወደ ታች በማውረድ የታለመለትን ግብ እንዲመታ በቁርጠኝነት እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡
በክልሉ ያለውን የትራንስፖርት ስርዓት በአግባቡ መምራት እንደሚገባ ጠቁመው÷ ለዚህም በቅንጅት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሀመድ÷ ቀደም ሲል ሲተገበር የነበረው የአሰራር ስርዓት በፖሊሲ የተደገፈ ካለመሆኑም በተጨማሪ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ሲደረግ የቆየው ነዳጅን በጅምላ የመደጎም አሰራር ለኮንትሮባንድ ንግድ በር የከፈተ እና ሀገሪቱንም በእዳ ጫና የዘፈቀ መሆኑን ተናግረዋል።
ተግባራዊ ሊደረግ የታሰበው የታለመ የነዳጅ ድጎማ አሰራር በተለይም በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኘውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸው÷ ሪፎርሙን በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ በሚከናወኑ ተግባራት ክልሎች ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ሀገሪቱ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ባደረገችው የነዳጅ ድጎማ 132 ቢሊየን ብር እዳ ያለባት ሲሆን÷ ይህም ከፍተኛ የእዳ ጫና ማስከተሉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.