Fana: At a Speed of Life!

ለአምባሳደሮች እና የኤጀንሲ ኃላፊዎች የብሔራዊ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ላይ ማብራሪያ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት ለአምባሳደሮች እና ለኤጀንሲ ኃላፊዎች በዘጠኝ ወራት የብሔራዊ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ላይ ማብራሪያ ተሰጠ ።
በመድረኩ የተሳተፉት የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ÷ ባለፉት ሁለት ዓመታት የሀገሪቱ ብሔራዊ ኢኮኖሚ ፈተና የነበሩ እና እስካሁንም ያልታለፉ መሰናክሎችን አንስተዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት እንዲሁም የድርቅ ክስተት ያስከተለውን ችግር ያስታወሱት ሚኒስትሩ ÷ በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መልካም የሚባል ውጤት ማሳየቱን አስረድተዋል።
በተለይም በወጪ ንግዱ እና በባንክ ስርዓቱ ዘርፍ ዕድገት መመዝገቡን ነው የተናገሩት ።
አጋር አካላት ይህንን የኢትዮጵያን ፅኑ እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ጉዞን እንዲደግፉም ጠይቀዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍፁም አሰፋ በበኩላቸው÷ ጥቅል የማክሮ ኢኮኖሚው የዘጠኙ ወራት ስኬቶች እና ችግሮችን የተመለከተ የመወያያ ፅሁፍ ለአምባሳደሮቹ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጪ ተፅዕኖዎች ስር ብትቆይም በዘጠኙ ወራት በየዘርፉ የማክሮ ኢኮኖሚው አፈፃፀም እና የዕድገት አመላካቾችን ጠቅሰዋል።
የሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት አጋርነትን አጠናክሮ በማስቀጠል በቀጣይም ለሃገር በቀል ኢኮኖሚ ዕድገት ልዩ ትኩረት ይሰጣል ነው ያሉት።
ለአምባሳደሮቹ እየተሰጠ ባለው የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ማብራሪያ ላይ÷ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ተሳትፈዋል።
በሶዶ ለማ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.