Fana: At a Speed of Life!

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ2 ሚሊየን ብር የማበረታቻ ሽልማት ተበረከተ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 9 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ2 ሚሊየን ብር የማበረታቻ ሽልማት ተበረከተለት።

ብሄራዊ ቡድኑ ትናንት የኒጀር አቻውን 3 ለ 0 ማሸነፋን ተከትሎ የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ ሽልማቱን ማበርከታቸው ተገልጿል።

ሽልማቱ ቡድኑ በቀጣይ የሚያደርጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ለአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ ለማበረታታት እና ለማነሳሳት  መሆኑ ተመላክቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ኮሚሽኑ ብሔራዊ ቡድኑ ትናንት ባስመዘገበው ውጤት ለቡድኑ የምሳ ግብዣ አድርጓል ።

የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር  አቶ ኤሊያስ ሽኩር በፕሮግራሙ ላይ÷ብሔራዊ ቡድኑ ትናንት ያሳየው ጨዋታ እና ያስመዘገበው ውጤት ትርጉሙ ትልቅ ነው ብለዋል ።

በተለይም ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ ቡድኑ የመጀመሪያውን ጎል አስቆጥሮ ተጫዋቾቹ ደስታቸውን የገለጹበት መንገድ ለመከላከያ ክብር እቆማለሁ በሚል መሪ ቃል በዕለቱ ከተካሄደው መርሃ ግብር ጋር ተያይዞ ትልቅ ትርጉም ነበረውም ነው ያሉት፡፡

አያይዘውም ቡድኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሰባስቦ እና ተገቢውን ልምምድ በማድረግ እንዲሁም ፌዴሬሽኑ ያመቻቸውን የወዳጅነት ጨዋታ ተጠቅሞ ያስመዘገበው ውጤት እንዳኮራቸውም ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በቀጣይ ብሔራዊ ቡድኑ ለሚያደርገው ጨዋታ እንደመንግስት እና ኮሚሽን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው÷ ብሔራዊ ቡድኑ ባስመዘገበው ውጤት መደሰታቸውን  ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.