Fana: At a Speed of Life!

ለከፍተኛ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የተደራጀ ቡድን ሊቋቋም ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ከፍተኛ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የተደራጀ ቡድን ሊቋቋም መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።
የሚቋቋመው ግብረ ሃይል ከህክምና፣ ፎረንሲክ፣ መረጃና ሌሎች ተቋማት የሚውጣጡ ባለሙያዎችን ያካተተ መሆኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመተባበር ቡድኑን መመስረት የሚያስችሉ አሰራሮችን ለመዘርጋት የሚያስችል ውይይት አካሂዷል።
በኢትዮጵያ የአውሮፕላን አደጋን ጨምሮ በሚከሰቱ ሌሎች ከባድ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ተጎጂዎችን የሚለይ “ዲዛስተር ቪክትም አይደንቲፊካሽን ቲም” እስካሁን አልተቋቋመም።
በዚህም ምክንያት ለአደጋ ፈጥኖ ያለመድረስ፣ ተቀናጅቶ አለመስራት፣ የዘረመል ምርመራ አለማድረግ እና ሌሎችም ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰዋል።
በመሆኑም በቀጣይ አደጋዎች ሲገጥሙ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ በአሰራር የተደገፈ ቡድን ማቋቋም ማስፈለጉን በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የፎሪንሲክ ምርመራ ምክትል ዋና ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ከተማ ደባልቄ ገልጸዋል።
የብሔራዊ ኢንተርፖል ሃላፊ ኮማንደር ጸጋየ ሃይሌ፥ ቡድኑ ከተለያዩ ሃገራት ልምድ ተወስዶ የሚቋቋም በመሆኑ በአደጋ ወቅት ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶችን የሚያስቀር መሆኑን ተናግረዋል።
የቡድኑ መቋቋም በሳይንሳዊ መንገድ የሰዎችን ማንነት መርምሮ ለመለየትና የአደጋን መንስኤ ለማጣራት ለሚደረገው ምርመራም አጋዥ ይሆናል ብለዋል።
ለዚህም ፌደራል ፖሊስ የዘረ-መል ምርመራ ለመጀመር የሚያስችል የባለሙያዎችና ላቦራቶሪ ዝግጅት አድርጓል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.