Fana: At a Speed of Life!

ለዘጠኝ የሃገር ውስጥ ሲቪል ማህበራት ምርጫውን እንዲታዘቡ ፈቃድ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሄራዊ ምርጫ ቦርዱ ለዘጠኝ የሃገር ውስጥ ሲቪል ማህበራት ምርጫውን መታዘብ እንዲችሉ ፍቃድ መስጠቱን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያ «የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011» እንዲሁም «የሀገር ውስጥ የምርጫ ታዛቢዎች ፍቃድ አሰጣጥ፣ አሠራር እና ሥነ-ምግባር መመሪያ ቁጥር 5/2012» በሚደነግገው መሠረት፣ ምርጫ ለመታዘብ ፍላጎት ያላቸውን የሀገር ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ይፋዊ ማስታወቂያ በማውጣትና በመመልመል በአንደኛ ዙር ለ36 ድርጅቶችን እውቅና መስጠቱ ይታወሳል፡፡

በተጨማሪም ምርጫውን መታዘብ እንዲችሉ በመጀመሪያው ዙር አመልክተው ካልተመረጡ የሀገር ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል ለቦርዱ ይግባኝ በማስገባት ይግባኛቸው በቦርዱ ታይቶ ውሣኔ ከተሰጠባቸው እና በሁለተኛ ዙር እንደ አዲስ ምርጫውን ለመታዘብ ማመልከቻ ካስገቡ ድርጅቶች መካከል ዘጠኙ ፈቃድ ማግኘታቸውን ገልጿል፡፡

በዚህ መሰረት

1. ማኅበረ ሕይወት ኢትዮጵያ – ፎር ሶሻል ዴቨሎፕመንት
2. አልቢር ዴቨሎፕመንት ኤንድ ኮኦፕሬሽን አሶሴሽን
3. ዲጂታል ሮግ ሶሳይቲ ኤክስፐርመንት ግሩፕ
4. ስፕሪድ የማኅበራዊ ችግሮች መፍቻ እና የልማት ድርጅት
5. የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር
6. ሰኔ 16 የሰላምና የለውጥ ተምሳሌት የሲቪክ ማኅበር
7. የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን
8. የአፍሪካ ልማትና ጥበቃ ተቋም
9. ሶሳይቲ ፎር ኢኮ ቱሪዝም ኤንድ ባዮ ዳይቨርሲቲ ኮንሰርቬሽን ፈቃድ ማግኘታቸውን የቦርዱ መረጃ ያመላክታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ድርጅቶች አዲስ የምርጫ መታዘብ ፈቃድን የሚጠይቅ ማመልከቻ ለቦርዱ እያስገቡ ይገኛል፡፡

ሆኖም ምርጫ የሚደረግበት ጊዜ እየተቃረበ በመምጣቱ ካለው በጣም የተጣበበ ጊዜ አንጻር ለቦርዱም ሆነ ለማህበራቱ ተገቢውን የዝግጅት ሥራ ለመከወን አዳጋች በመሆኑ ምክንያት ይህ ማስታወቂያ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የሚቀርቡ የመታዘብ ሥራ ጥያቄዎችን ቦርዱ መቀበል ማቆሙንም ነው ያስታወቀው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.