Fana: At a Speed of Life!

ለደቡብ ክልል ግንባር ቀደም ግብር ከፍዮች እውቅና ተሰጠ

 

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 14 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የደቡብ ክልል ለግንባር ቀደም ግብር ከፍዮች እውቅና ሰጠ።

እውቅና እና ሽልማቱን የሰጡት የደቡብ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባሄ ወይዘሮ ሄለን ደበበ ÷የኮሮና ቫይረስ ተፅእኖን በመቋቋም በታማኝነት ታክስና ግብራቹን ስለከፈላቹሁ የክልሉ መንግስት ያመሰግናችኋል ብለዋል ።

ሀገራዊ ለውጡን እውን ለማድረግ የፍይናንስ ሀብት ማሰባሰብ ይጠበቃል ያሉት አፈ ጉባሄዋ ÷ ከብድርና እርዳታ ለመላቀቅም ታማኝ ግብር ከፍዮችን ማፍራት ይገባልም ነው ያሉት ።

እውቅና የተሰጣቸው ግብር ከፍዮች በቀጣይም በገበታ ለሀገር ፕሮጀክትና የህዳሴ ግድቡን ለማጠናቀቅ ድጋፍቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል ።

የክልሉ የገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ዘይቱና ኢብራሂም በበኩላቸው ÷እስከ 6 ሚሊየን ብር ድረስ ግብርና ታክስ የከፈሉ ታማኝ ግብር ከፍዮችና ለህግ ተገዢ የነበሩ ከደረጃ ሀ እስከ ሐ ያሉ 89 ግንባር ቀደም ግብር ከፍዮች እውቅና ተሰቷቸዋል ብለዋል ።

በየግንባር ቀደም ግብር ከፍዮች የእውቅና ስነ ስርአት ላይ 90 ሚሊየን ብር ግብርና ታክስ የከፈሉ የመንግስት የልማት ድርጅቶችም እውቅና ተሰቷቸዋል ።

ከፋና ጋር ቆይታ የነበራቸው ተሸላሚ ግብር ከፍዮቹ የንግድ ስራው በኮሮና ቢቀዛቀዝም በታማኝነት ግብራችን ከፍለናል ፣ እውቅናው ለተሻለ ስራም የሚያነሳሳን ነው ብለዋል ።

ክልሉ በተጠናቀቀው የግብር ዘመን 10ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ሰብስቧል ።

በሀይለየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.