Fana: At a Speed of Life!

ለጋሾች በየመን በሃውቲ ቁጥጥር ስር በሚገኙ ይዞታዎች የሚያደርጉትን ሰብአዊ እርዳታ እንደሚቀንሱ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለጋሾች በየመን በሃውቲ አማጽያን ቁጥጥር ስር በሚገኙ ይዞታዎች የሚያደርጉትን ሰብዓዊ ድጋፍ ሊቀንሱ እንደሚችሉ አስታወቁ።

ለዚህም በአካባቢው ያለው ሁኔታ ለስራቸው እንቅፋት መሆኑን ገልጸዋል።

በአካባቢው ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ሳቢያም ሰብዓዊ ድጋፉ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በአግባቡ እየደረሰ አይደለምም ነው ያሉት ለጋሾቹ።

በሰሜን የመን የሚገኙ የአማጺ ቡድን መሪዎች በአካባቢው የሚኖሩና በእርዳታ ላይ ጥገኛ ለሆኑ የመናውያን የሚደረጉ የምግብና ሌሎች እርዳታዎች በአግባቡ እንዳይደርሱ መሰናክል እየፈጠሩ ነው ተብሏል።

ይህን ተከትሎም ሁኔታዎች የማይስተካከሉ ከሆነ ከቀጣዩ ወር ጀምሮ የሚደረገው ሰብዓዊ እርዳታ ይቀንሳል ነው ያሉት።

ሊቀንስ ይችላል የተባለው ሰብዓዊ ድጋፍ በመንግስታቱ ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም የሚቆጣጠረውና በወር ከ12 ሚሊየን በላይ ሰዎችን የሚመግበውን ድጋፍ ያካትታል።

በየመን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰ የመጣው ግጭትና መሰል ሁኔታዎች የረድኤት ድርጅቶች በሙሉ አቅማቸው ድጋፍ እንዳያደርጉ እንቅፋት መፍጠሩ ይነገራል።

ምንጭ፦ ሬውተርስ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.